ኢሳት ዜና (ነሐሴ 12 ፣ 2007)
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንጌ ወረዳ የመንግስት ሃይሎች አርብ እለት በሰነዘሩት ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ። ከሟቾቹ ውስጥ 5ቱ ህይወታቸው ያለፈው እስር ቤት ከተወሰዱ በኋላ በምግብ ተመርዘው እንደሆነ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አስታወቀ።
የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ሊቀመመንበር አቶ አብዱልዋህድ መሃዲ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት አርብ ነሐሴ 8 ቀን 2007 የመንጌ ወረዳ ነዋሪዎች በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ምሬት በሰላማዊ ሰልፍ የገለጹ ሲሆን፣ በአካባቢው ተሰማርቶ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ በከፈተው ተኩስ 12 ሰዎች ሲገደሉ፣ 56 ሰዎች ቆስለዋል። 5ቱ ደግሞ በእስር ቤት ተመርዘው ሞተዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አባትና ልጅ እንዲሁም ወንድማማቾች እንደሚገኙበት አቶ አብዱልዋህድ መሃዲ በዝርዝር ገልጸዋል።
ህዝብ ላይ በሚደረገው የሃይል እርምጃ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ወቅትም መታየቱን የገለጹት የቤሕነን ሊቀመንበር አቶ አብዱልዋህድ መሃዲ፣ በወቅቱ 2 ሰዎች መገደላቸውን፣ የራሳቸውን አባት ጨምሮ በርካታ አዛውንቶች የተካተቱበት 54 ሰዎች መታሰራቸውንን ገልጸዋል።
80 አመት ያለፋቸው የእርሳቸው አባት ጨምሮ ለ 54ቱ ሰዎች መታሰርና አሁንም ድረስ በእስር ቤት መቆየት ምክንያት የሆነው በምርጫ ወቅት ህዝብ የክልሉን ገዢ ፓርቲ እንዳይመርጥና በምርጫው እንዳይሳተፍ ተሳትፋችኋል የሚል እንደሆነም ተመልክቷል።
አርብ እለት የተካሄደው ግድያ የዚያ ቀጣይ እንደሆነ የገለጹት የቤሕነን ሊቀመንበር፣ የተጠቀሰው የሟቾች ቁጥር የታወቀውና በስም የተረጋገጠው እንጂ ከዚያ የበለጠ ሰው ሊሞት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የቆሰሉት 56 ሰዎች በመንጌ ወረዳ በአሶሳ ሆስፒታል በህክምና ላይ መሆናቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
በቤኒሻንጉል ክልል መንጌ ወረዳ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ያረጋገጡ ሲሆን በመንግስት ወገን የተሰጠ መግለጫ የለም።