በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሱዳን ድንበር ዙሪያ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል መሰማራቱ ተነገረ

ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የድንበር ዙሪያ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል በማሰማራት ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኗን የመከላከያ ሰራዊት አርብ አስታወቀ። የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ በአካባቢው ወታዳራዊ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱም ይታወሳል።

ባለፈው ወር መንግስት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው የአባይ ግድብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 13 ታጣቂዎች ገደልኩ ሲል መግለፁ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት ተጨማሪ የጸጥታ ሃይልን በድንበር ዙሪያ በማሰማራት ከሱዳን መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የመከላከያ ሰራዊት 12ኛ ክፍለጦር ሃላፊ የሆኑት ኮሎኔል አረጋዊ ኪዳኔ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በአዲስ መልክ ተሰማርቶ የሚገኘው ይኸው የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የድንበር ዙሪያ የ24 ሰዓት የጸጥታ ጥበቃን እንደሚያከናውኑ ታውቋል።

በመገንባት ላይ ላለው የአባይ ግድብ ጥበቃን እያደረገ ያለው ይኸው ሃይል ከሱዳን የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ጋር በመቀናጀት የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እየተከታተለ እንደሚገኝ ወታደራዊ ሃላፊው አክለው አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ የተባለ አማጺ ቡድን በክልሉ ለረጅም ጊዜ የትጥቅ ትግልን እንደሚያካሄድ ብሉምበርግ የዜና ወኪል ባለፈው በአካባቢው ተፈጽሟል የተባለውን የመንግስት ጥቃት አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዲጠናከር መደረጉን ቢያሳውቅም የጸጥታ ስጋት ስለሆነው አካል የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

ኢትዮጵያና ሱዳን በተያዘው ሳምንት በአዲስ አበባ ባካሄዱበት የመሪዎች ውይይት የድንበር የጸጥታ አካባቢያቸውን በጋር ለመከላከልና በቅንጅት ለመስራት አዲስ ስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዲጠናከር መደረጉን ቢያሳውቅም፣ የጸጥታ ስጋት ሰለሆነው አካል የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

ኢትዮጵያና ሱዳን በተያዘው ሳምንት በአዲስ አበባ ባካሄዱት የመሪዎች ውይይት የድንበር የጸጥታ አካባቢያቸው በጋራ ለመከላከልና በቅንጅት ለመስራት አዲስ ስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ለአባይ ግድብ ግንባታ እየተደረገ ነው የተባለው ጥበቃ የዚህ ስምምነት አካል ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።