ኢሳት (ጥር 30 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በባንክ እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ እንዳይኖራቸው ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በርካታ ባንኮች በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ስር የነበሩ አክሲዮኖች ለጨረታ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ አክሲዮን የነበራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ የያዙትን አክሲዮን እንዲመልሱ ማሳሰቢያን አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
የጊዜ ገደቡን መጠናቀቅ ተከትሎም አዋሽ ባንክ በበርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስር የነበሩ 21ሺ 52 አክሲዮኖችን ለጨረታ ያቀረበ ሲሆን፣ ጨረታው በቀጣዩ ሳምንት እንደሚካሄድ አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
የንብ ባንክ በበኩሉ ወደ ስምንት ሺ አካባቢ የሚጠጉ አክሲዮኖችን በተመሳሳይ መልኩ ለጨረታ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል። ይሁንና በባንኩ አክሲዮን ገዝተው የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ሰርቲፊኬታቸውን መመለስ በነበራባቸው የጊዜ ገደብ ሳይመልሱ መቅረታቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።
የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መመሪያ የአክሲዮን ስርቲፊኬታቸውን የማይመልሱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮናቸው ለሽያጭ እንደሚቀርብ እና ገንዘቡም ተቀማጭ እንደሚሆን መወሰኑ ይታወሳል።
እስከ ሰኔ ወር ድረስም ባለድርሻ አካላት የተቀመጠላቸው ገንዘብ እንዲወስዱ በመመሪያው የተቀመጠ ሲሆን፣ ከሰኔ ወር በኋላ ግን ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም። በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ ያልቻሉ የአክሲዮኖች ባለቤቶች ስርቲፊኬታቸውን ሳይመልሱ መቅረታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
አክሲዮናቸውን እንዲመልሱ የተደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው መንግስት ያስተላለፈው ውሳኔ ለኪሳራ እንደዳረጋቸውና መመሪያው ፍትሃዊ አለመሆኑን ይገልጻሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳይሳተፉ መደረጉ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 16 የግል ባንኮችና የተወሰኑ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ተቋማት የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው ታውቋል።
የብሄራዊ ባንክ በበኩሉ ለሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያሉ የአክሲዮን ድራሻዎች ሙሉ ለሙሉ እስኪመለሱ ድረስ ምን ያህል ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻን ይዘው እንደሚገኙ እንደማይታወቅ አመልክቷል።
ይሁንና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተያዙ የአክሲዮን ድርሻዎች ወደ 40 ሚሊዮን ብር አካባቢ እንደሚገመት ይገልጻሉ።