በባቡር ፕሮጀክት ሥም የመስኖ መሬታቸውን ካለተመጣጣኝ ክፍያ መነጠቃቸውን የተሁለደሬ ወረዳ የጎበያ 012 ቀበሌ አርሶ አደሮች ተቃወሙ

በባቡር ፕሮጀክት ሥም የመስኖ መሬታቸውን ካለተመጣጣኝ ክፍያ መነጠቃቸውን የተሁለደሬ ወረዳ የጎበያ 012 ቀበሌ አርሶ አደሮች ተቃወሙ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ/ም) ነዋሪነታቸው በደቡብ ወሎ ዞን በተውለደሬ ወረዳ 012 ቀበሌ ልዩ ቦታው ጎበያ ገ/ማኅበር በመባል በሚጠራው ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች በመስኖ የሚለማ መሬታቸውን በባቡር መንገድ ዝርጋታ ምክንያት በርካሽ ዋጋ እንዲለቁ መደረጋቸውን 34 አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞ አሰምተዋል።
አርሶ አደሮቹ ተመጣጣኝ ካሳና ተለዋጭ የእርሻ መሬት ሳይሰጣቸው በሶስት ዓመት የደረቅ መሬት ሂሳብ በካሬ 43 ብር ተተምኖ እንዲለቁ መባላቸውን ይናገራሉ። የእርሻ ማሳቸው ላይ አፈር፣ አሸዋና ዲንጋይ የሚቆለልበት ስለሆነ ዳግም ሰብል ማብቀል እደማይችል ከግምት ሊጋልን ይገባልም ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ መንግስት መሬታቸውን ለልማት ከፈለገው ለመስጠት ፈቃደኞች መሆናቸውን ይናገራሉ። መሬቱ በመስኖ የሚለማና ማሳው ላይ ባህር ዛፍ፣ ጫትና የተለያዩ አትክልቶች የሚያበቅል በመሆኑ ቢያንስ የአስር ዓመት ተመጣጣኝ ካሳ ተተምኖ ይሰጠን ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ ያቀረቡትን ቅሬታዎች በመስማት መስተዳድሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ”መሬታችሁን ብታስለኩ አስለኩ፤ ካላስለካችሁና የምንሰጣችሁን ካልወሰዳችሁ በግዴታም ቢሆን በፌደራል ፖሊስ እናስነሳችኋለን” በማለት የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘውዱ ስለሺ ሰብስበው እንዳስፈራሯቸው አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።
መሬት ማለት የአርሶ አደር የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ በደረቅ መሬት ሂሳብ ተተምኖ መከፈል የለበትም በሚለው አቋማቸው አሁንም መጽናታቸውንና የሚመለከታቸው አካላት ችግራቸውን አውቀው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጧቸው ተማጽኖ አሰምተዋል።