(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2010) በሶማሌ ክልል የልዩ ሐይል አባላት በኦሮሚያ ባሌ ዞን ሕጻናትን ጨምሮ 5 የአንድ ቤተሰብ አባላትን መገደላቸው ተነገረ።
በሌላ ዜና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ በኦሮሚያ ክልል በሶስት አቅጣጫ ገብቷል በሚል በክልሉ አሰሳ እና እስራት መጠናከሩን ምንጮች ለኢሳት ገለጸዋል።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ በነገሌ ቦረና ዞን ማክሰኞ ሌሊት የተጀመረው አሰሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከሞያሌ በ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ የተንቀሳቀሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ ያሬሮ የገቡ ሲሆን ፣ቤት ለቤት ጭምር አሰሳ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
አሰሳው በቦርቦር፣ዋጨሌ ፣አደርቢ ጭምር እንደሚቀጥልም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከሞያሌ ከተማ በብዙ ኪሎሜትር ርቀት ላይ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ሁለት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውንና የሰራዊት አባላት መገደላቸውን ተከትሎ ሞያሌ ከተማ ውስጥ በሲቪሎች ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ በወሰደው የበቀል ርምጃ በትንሹ 13 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
አሁንም በነገሌ ቦረና አሰሳ የወጣው ሃይል በሰላማዊ ነዋሪው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በአካባቢው ከፍተኝ ስጋት መኖሩንም መረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንቅስቃሴ ታይቶበታል በተባለው ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ አፈሳ ሊባል በሚችል መልኩ ሰላማዊ ነዋሪዎች በመታሰር ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በነቀምት፣ሻምቡ፣ደምቢዶሎ እስራቱ መጠናከሩንም ለመረዳት ተችሏል።
በተለይ በደምቢዶሎ ገርጄዳ እና ላሎጋሪ በተባለ ቦታ ባለፈው ረቡዕ ቀኔሳ ድንገታ እና ሙሉጌታ ድንገታ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ በአንድ ቀን አስር ሰዎች ታስረዋል።
ወንድሙ ቦጃ፣ሚካኤል ደበላ፣መሰረቱ ቡረሴ ፣ምስጋኑ ኢተፋ፣ ጫላ ሹማ ፣ሚካኤል ሃይሉ እና ፈይሳ ሙጬ ከታሳሪዎቹ ውስጥ እንደሚገኙበትም መረዳት ተችሏል።
በሌላ ዜና የክልል ሚልሻ እና ፖሊስ ጭምር በኮማንድ ፖስቱ ዕዝ ውስጥ መሆኑ በተገለጸበት በአሁኑ ወቅት ሕጻናትን ጨምሮ 5 የአንድ ቤተሰብ አባላት በባሌ ዞን ውስጥ ትናንት በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል መገደላቸው ታውቋል።
በባሌ ዞን በሰዌና ወረዳ ቡርቃ ጠሬ በተባለ መንደር ሶስት ሕጻናትን ጨምሮ የአንድ የቤተሰብ አባላት መገደላቸውን የዘገበው ቪኦኤ ነው።
በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል የተፈጸመውን ግድያ የወረዳው አስተዳዳሪም አረጋግጠዋል ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እና የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ አቶ አሰፋ አብዩ በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ የክልል ሚልሻ፣ የክልል ፖሊስ እና ልዩ ሃይል ጭምር በኮማንድ ፖስቱ ዕዝ ውስጥ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ ስለዚህ አሰቃቂ ግድያ እስከአሁን የሰጠው መግለጫ የለም።