መጋቢት ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢ ተቆርቋሪና የማህበረሰብ ቱሪዝም ኤክስፐርት የሆነው ወጣት ቢኒያም አድማሱ ሰሞኑን በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እንደተቀሰቀሰ መስማቱን ተከትሎ ወደዚያው በማቅናት እሳቱን ለማጥፋት ሲረባረብ ነው በቃጠሎ ህይወቱ ያለፈው።
ወጣት ቢኒያም ወደባሌ ብሄራዊ ፓርክ ያቀናው እንደሱ እሳቱን ለማጥፋት ከዘመቱ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሰባሰብ ነበር። በስፍራው ደርሰው በጋራ ርብርብ በሚያደርጉበት ወቅት እሳቱ ቢኒያምን ጨምሮ ሌሎቹን ወጣቶች በመክበብ ቀለበት ውስጥ እንዳስገባቸው የተናገሩት ምንጮች፤ እሳቱ ቢኒያምን እንደደረሰበትና ለህልፈት እንደዳረገው፣ ከእርሱ ሁዋላ በነበረ አንድ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት እንዳደረሰ እና ሌሎቹ ለማምለጥ መቻላቸውን አመልክተዋል።
በፍራንክፈርት የእንስሳት ጥናት ማህበር ውስጥ የሚሰራው ወጣት ቢኒያም፤ታዋቂ የአካባቢ ተቆርቋሪና የኢኮ ቱሪዝም ባለሙያ ሲሆን፤ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጀምሮ በደቡብ እስከሚገኘው እስከ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ድረስ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙትን ብሄራዊ ፓርኮች ያለመታከት ሲያስተዋውቅ የኖረ ወጣትነበር ነው።