በባህር ዳር ጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ አራት አባላት ተገደሉ

ኢሳት (ነሃሴ 3 ፥ 2008)

በባህር ዳር ከተማ በሚገኝ አንድ የመከላከያ ካምፕ ውስጥ ሰኞ በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ የእርስ በዕርስ ግጭት በትንሹ አራት አባላት መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

በከተማዋ አለመረጋጋት መኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ አባላቱ ሊገደሉ መቻላቸውንና ድርጊቱ አዲስ ውጥረት ማንገሱን አስረድተዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ እስከ ማክሰኞ ድረስ የግልም ሆነ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ አለመጀመራቸው ታውቋል።

የመንግስት ባለስልጣናት ነዋሪው መደበኛ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል በማግባባት ላይ ቢሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች የተለያዩ ተቃውሞዎችን በማሰማት ትዕዛዙን ተግባራዊ አለማድረጉን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ኤኢሳት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በጎንደር ከተማ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን ያልጀመሩ ሲሆን፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጨለማን ተገን በማድረግ ነዋሪዎችን በማሰር ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የዞንና የቀበሌ አስተዳደሮች ነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል በማግባባት ላይ ቢሆኑም ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥሪውን እንዳልተቀበሉ ምንጮች ገልጸዋል።