በባህር ዳር ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከተቃጠሉ የመኪና ጋራዥ ባለቤቶች አንዱ በቃጠሎው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)

በባህር ዳር ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከተቃጠሉ የመኪና ጋራዥ ባለቤቶች አንዱ በቃጠሎው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ። የትግራይ ተወላጅ የሆኑትና በባህር ዳር ከተማ ለረጅም አመታት የኖሩት በህዝብ ዘንድ አለሙ ገንዳ በሚል የሚታወቁት አቶ አለሙ ካህሳይ የታሰሩት በሳምንቱ መጀመሪያ ነው።

ግለሰቡ የተጠረጠሩትና ለእስር የተዳረጉት ባለፈው ቅዳሜ የአመፅ ወረቀት ሲበትኑ መያዛቸውን ተከትሎ መሆኑንም መረዳት ተችሏል። አቶ አለሙ ካህሳይ ባለፈው ቅዳሜ “ትግሬዎች ተነሱ” የሚል ወረቀት ሲበትኑን በተመረጡ ሰዎች ቤት ሲያድሉ አለበል ካሴ በተባሉ የክልሉ ባለስልጣን እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ ጋራዡንም ራሳቸው ስለማቃጠላቸው መረጃ  መገኘቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ አለሙ ካህሳይ ወይንም አቶ አለሙ ገንዳ ከጋራዥ በተጨማሪ የቤት እቃዎች ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል ለሚገኙ በርካታ ት/ቤቶች የመማሪያ ጠረጴዛና ወንበር እንዲያቀርቡ ልዩ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱንም ምንጮች ገልጸዋል።

ሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ አለሙ ካህሳይ ጋራዡን ያቃጠሉት ከኢንሹራንስ ጋር በተያያዘ ለሚገኝ ካሳ ይሁን በሌላ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ለትግራይ ተወላጆች “እንነሳ” የሚል ወረቀት ሲበትኑ መገኘታቸው ግለሰቡ ድርጊቶቹን የሚፈጽሙት በተቀነባበረ መንገድ በድርጅታዊ መዋቅር ይሆናል የሚል ጥርጣሬ መጋበዙም ተመልክቷል።

ግለሰቡ ድርጊቱን የሚፈጽሙት በህወሃት መመሪያ ከሆነ፣ ግለሰቡ ሲታሰሩ ህወሃቶች እንዴት ዝም አሉ የሚል ጥያቄ እየተነሳ ሲሆን፣ በድርጊቱ አፈጻጸም ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች በግልጽ የታወቀ ምላሽ የለም።

ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አቶ አለሙ ካህሳይ ወይንም አለሙ ገንዳ ንብረት በማውደም እንዲሁም የዘር ቅስቀሳ በማድረግ ተወንጅለው በምርመራ ላይ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።