ታኀሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለምዶ የመስቀል አደባባይ ተብሎ የሚጠራውን የታቦት መውረጃ ቦታ ለግል ባለሃብቶች ለመሸጥ ታስቧል በሚል ሰሞኑን እንቅስቃሴ በጀመረው የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የከተማ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ድርጊት የተቆጡት የከተማዋ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እና በፖሊስ መካከል በተነሳው ግጭት ከ 3-5 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያስረዳል፡፡ 27 ሰዎች ታስረው እየተደበደቡ ነው።
የእምነቱ ተከታዮች በከተማው መካከል በሚገኘው የቀድሞው የክልሉ ምክር ቤት ህንጻ በመሄድ አቤቱታቸውን ለክልሉ መንግስት ሊያቀርቡ ቢሞክሩም በአካባቢው የተሰባሰቡት ፖሊሶች ህዝቡን ለመበተን ጥይት በመተኮስ ጉዳት ማድረሳቸውን ያይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
በሺዎቹ የሚቆጠሩት የእምነቱ ተከታዮች አባይ ዳር በተሰራው አዲሱ የክልሉ ምክር ቤት ህንጻ በመሰባሰብ ልዩልዩ መንፈሳዊ መዝሙሮችን በማሰማት ዙሪያውን የከበቡ ሲሆን ከጠዋት ጀምሮ ከጎንደር መስመር የሚመጡም ሆነ ወደ ጎንደር መስመር የሚሄዱ መኪኖች የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች እስከ ቀኑ ስምንት ሰአት ድረስ ቦታውን አንለቅም በማለት በአዲሱ ክልል ምክር ቤት ዙሪያ ከበው ውለዋል፡፡የከተማ አስተዳደሩህዝቡ ካልተስማማ ግንባታውን እናቆማለን ቢልም ምእመኑ ግን ይህን የሚያስረዳ ማረጋገጫ በጽሁፍ እስካልተሰጠን ድረስ ከቦታው አንንቀሳቀስም በማለት ለሰአታት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
የከተማ መስተዳድሩ በመኪና እየዞረ የማፍረሱን ስራ ትቸዋለሁ በማለቱ አመጹ ለጊዜው መብረዱን የሚናገሩት ወገኖች፣ መስተዳድሩ ቦታውን ለግንባታ ለመሸጥ እንቅስቃሴ ከጀመረ ግን ተመሳሳይ ተቃውሞ ሊነሳ እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
መስተዳድሩ በተጠቀሰው ቦታ ላይ መንገድ ለመስራት እንጅ ቦታውን ለባለሃብት ለመሸጥ አላሰብኩም በማለት መናገሩን የመስተዳድሩን መግለጫ የተከታተሉት ዲያቆን ዘላለም ታከለ ለኢሳት ተናግረዋል
ይሁን እንጅ ከአዝዋ ሆቴል ተነስቶ ወደ ሙሉአለም የባህል ማእከል የሚያልፈዉ መንገድ ሲሰራ ታቦተ ፅላቱ የሚያርፍበትና የመስቀል የደመራ በአል የሚከበርበት መስቀል አደባባይ 7 ሜትር ያህል ቦታ ሊወሰድ እንደሚችል ታውቋል።
ተቃውሞ ለማሰማት ወደ ምክር ቤት የገቡ 5 ሰዎች በጠባቂ ፖሊሶች መገደላቸውን የፌደራል ፖሊስ ለመንግስት ባለስልጣናት ሪፖርት ማድረጉን በመጥቀስ የባህርዳሯ ወኪላችን ገልጻለች ። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የማቾች ቁጥር 3 ነው ይላሉ። ፌደራል ፖሊስ ሰልፈኛውን ለማስቆም የተወሰደ እርምጃ ነው ብሎአል። ይሁን እንጅ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ከመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም።
ማምሻውን ደግሞ ፖሊሶች ከቤት ወጣቶችን እያወጡ እያፈሱ በማሰር ላይ ናቸው። የፌደራል ፖሊሶች ከወረታና ከጎንደር መምጣታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። በተቃውሞው ላይ አንድ የአካል ጉዳተኛም መደብደቡን እህቱ ለኢሳት ገልጻለች