ኅዳር ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች በሚደረጉ ፍተሻዎች ነዋሪው እየታወከ መሆኑን በባህርዳር የጣናና ሽምብጥ ክፍለከተማ ነዋሪዎች ለኢሳት ተናገሩ፡፡
በውድቅት ሌሊት የመንግስት ወታደሮችና ታጣቂዎች በወደ ግለሰቦች ቤት በመግባት ‹‹ፍተሻ እናካሂዳለን!!›› በማለት ከሌሊት እስከ ንጋት ድረስ ሲያንገላቷቸው ያድራሉ፡፡በተለይ በጣና ክፍለ ከተማ ቀጠጢና በተባለ መንደር የሚገኙ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት ወደ ሆቴል ቤት የምግብ ስራ ለመስራት የሚጓዙ ሰራተኞችን በማስቆም እያጉላሉ ሲሆን፣ ሴት ልጆችን በማንገራገርና በማንገላታት ‹‹መሳሪያ ለማን ልታቀብሉ ነው በዚህ ሰዓት የምትንቀሳቀሱት?››በማለት ከፍተኛ በደል እየፈጸሙባቸው መሆኑን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በሽምብጥ ክፍለ ከተማ ወራሚት በተባለ መንደር ነዋሪ የሆኑ በጫት ንግድ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች እንደተናገሩት ‹‹ወታደሮቹ መሳሪያ አላችሁ አስረክቡ!!›› በማለት ሲያንገላቷቸው እንደሚያድሩ በምሬት ተናግረዋል፡፡ለመብታቸው የሚከራከሩ ነዋሪዎችን እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ይወስዳሉ። የገዥው መንግስት ወታደሮች በቤት ውስጥ ፍተሸ ሲያካሂዱ የቤት እቃዎችን በመሰባበር እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የእህል ማስቀመጫ ጎተራዎችን፣የልብስ ማስቀመጫ ሳጥኖችንና በሁሉንም የቤት ዕቃዎች ውስጥ የተደበቀ መሳሪያ ወይንም ጥይት ለማግኘት በሚል ከፍተኛ እንግልት ያደርሱባቸዋል።
በሌላ በኩል ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ሲጠናቀቅ 10 ነባር አመራሮችን በማስቀጠልና 12 አዳዲስ አመራሮችን በመምረጥ ቢያጠናቅቅም፣ አዲሶችም ሆኑ ነባር አመራሮች ራሳቸውን ከህውሃት አመራር ነጻ አድርገው መስራት የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ተሿሚዎችን በቅርበት የሚያውቁዋቸው ሰዎች ይናገራሉ።
በነሃሴ ወር በባህርዳር ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ የአገዛዙ ወታደሮች ባደረሱት እልቂት የመስሪያ ቤት ዘበኞችን በማሰማራት ተሳታፊ እንደነበሩ በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ወይዘሮ ገነት ገብረእግዚአብሄር ተመልሰው መሾማቸው፣ እንዲሁም የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሹመት ያገኙት አቶ ፍስሃ ወልደሰንበት የህውሃት ዋና ቀኝ እጅ በመሆን እንደሚሰሩ እየታወቀ ፣ የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ሆነው መመረጣቸው ህወሃት ክልሉን በራሱ ሰዎች ለመቆጣጠር የዘረጋውን እቅድ የሚያሳይ ነው በማለት ምንጮች ተናግረዋል።