በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ እምቢተኝነት  የተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ወጣቶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንዳስከፋቸው የወጣቶቹ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡

መስከረም ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከባህር ዳር ከተማ በመንገድ ላይ ሲዘዋወሩ የተያዙትን እነዚህ ወጣቶች ከባህር ዳር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የወንዳጣ እስር ቤት ታጉረው ከሰነበቱ በኋላ፣  የስርዓቱ ቃል አቀባይ በሆኑ ና አብረው የታሰሩ በመሰሉ ከሃዲዎች ተገኘ በተባለው መረጃ ብቻ ተመርጠው ወደ ብር ሸለቆ ወታደራዊ የጦር ካምፕ ማሰልጠኛ ተወስደው በከፍተኛ ስቃይ ላይ መሆናቸውን ከስፍራው በሚወጡ መረጃዎች መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹን በወንድአጣ እስር ቤት መጀመሪያ ካጎሩ በኋላ አብረው በጥፋታቸው የታሰሩ በማስመሰል ደህንነቶችን በማስገባት እያንዳንዱ ወጣት የሰራውንም ያልሰራውንም  እንደ ጀብዱ እንዲያወራ በማድረግና ሰራሁ ያለውን በመመዝገብ ባቀረቡት ሪፖርት ወጣቶቹ በጥፋተኝነት መፈረጃቸውን ወላጆች ተቃውመዋል፡፡ወጣቶች ከሃዲ ይኖራል በማለት ሳያስቡ ያላደረጉትን እንዳደረጉ በየዋህነት ማውራታቸው እንደፈጸሙት ተቆጥሮ በጥፋተኝነት ከሰብአዊነት ውጭ በሆነ መልኩ መቀጣታቸው አግባብ አለመሆኑን ወላጆች ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በተሰባበሩ ጠርሙሶች ላይ በባዶ እግራቸው  እንዲሄዱ በማድረግ ከፍተኛ ስቃይ እንዲሰማቸው እየተደረገ ሲሆን ፣ ከአራት መቶ በላይ በሆኑ ወጣቶች ላይ ግርፋትና ልዩ ልዩ ስቃዮች እየተከናወነባቸው መሆኑን ከአካባቢው ከመጡ የአይን እማኞች መረዳታቸውን ወላጆች በቁጭት ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡