በባህርዳር ፖሊሶች አንዷን እስረኛ ከእስር ቤት አውጥተው ደፈሯት

በባህርዳር ፖሊሶች አንዷን እስረኛ ከእስር ቤት አውጥተው ደፈሯት
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ/ም) በባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ እመቤት አዳነ የተባለች በጥርጣሬ የታሰረችን እስረኛ የምሽት ተረኛ ጠባቂዎች ከእስር ቤት በማውጣት አስገድደው ደፍረዋታል።
እስረኛዋ ለጣቢያው የምርመራ ክፍል ሃላፊ ም/ኢንስፔክተር ፋጡማ ማሩ ብታመለከትም ኢንስፔክተሯ ድርጊቱ የፖሊስን ገጽታ የሚያበላሽ ነው በማለት ተራኛ ፖሊሶቹ በህግ እንዳይጠየቁ ለማድረግ እየተከላከለች እንደምትገኝ ታውቋል። አቤቱታው ለዞን ፖሊስ መምሪያ ቢቀርብም በዞኑ በኩልም እስካሁን መልስ አልተሰጠም።
እስረኛዋም የተፈጸመባትን በደል የምታሰማበት አካል ማጣቷን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በቅርቡ በይልማ ዴንሳ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ከእስረኞች ማደሪያ ግቢ ውስጥ ተረኛ የሆነው ፖሊስ ኮንስታብል እረታ እሸቱ በእስር የነበረችን የ22 ዓመቷን ግለሰብ አዲሴ እሸቴን ሚያዚያ 13 ቀን 2010 ዓም ከእስር ቤት አውጥቶ በመሳሪያ በማስፈራራት፣ በመደብደብ ከጥበቃዎች ማደሪያ ክፍል ውስጥ በማስገባት አስገድዶ መድፈሩን ተከትሎ ፍርድ ቤት በ2 አመት ከ3 ወር ቀላል እስራት እንደፈረደበት የይልማ ዴንሳ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ይፋ አድርጎ ነበር። የቅጣቱ ማነስን የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ሲገልጹ ሰንብተዋል።