በባህርዳር ድሆች መኖሪያ ቤታቸውን እየተቀሙ ለጎዳና ተዳዳሪነት ተዳርገዋል

መስከረም ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የድሃ ድሃ ተብለው ተመርጠው ኑሮቸውን በጉስቁልና የሚመሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከደርግ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድርስ በቀበሌ ቤቶች ሲገለገሉ ቢቆይም ያለ አግባብ በባለስልጣናት እየተቀሙ መሆኑ ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጡ እንዳደረጋቸው ነዋሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት ደሀዎችን “ተተኪ ቦታና ቤት ይሰጣችሁዋል” በማለት ቤቶችን እየቀሙ ለባለሐብቶች እና ለራሳቸው በሊዝ እየገዙ አዳዲስ ህንጻዎችን መገንባታቸውን ተከትሎ ድሆች ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ግድ እንዳለ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል።

ችግሩ እንዲፈታላቸው ለመንግስት አካላት ለአመታት አቤት ቢሉም ምንም መፍትሄ እንደላገኙ ይናገራሉ። አንዳንዶች ቤታቸው ከፈረሰባቸውና ጎዳና ላይ ማደረግ ከጀመሩ 5 አመታት አልፎአቸዋል፤ ካሳ ወይም ተተኪ ቤት አለማግኘታቸውን በምሬት ይገልጻሉ።

በመላ አገሪቱ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።