በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የተካሄደው ተቃውሞ የተሳካ እንደነበር መምህራን ገለጹ

መስከረም ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- መምህራኑ በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ የተጠቀሙበት የዝምታ ተቃውሞ፣ ገዢው ፓርቲ ያሰበውን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውል ስራ እንዳይሰራ አድርጎታል።

‹‹ በዝምታ ተቃውሞን መግለጽ!! ››  በሁሉም የስብሰባ አዳራሾች ተግባራዊ በመሆኑ፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ንዴታቸውን ለመቆጣጠር ያልቻሉበት ሁኔታ መከሰቱን ያወሱት መምህራኑ፣ በመጀመሪያው  ቀን ምንም አይነት አስተያየት ከመድረክ ያልተሰጠ ሲሆን፣ በሁለተኛ ቀን በተደረገው ስብሰባም ከተሰብሰቢው ሳይቀርቡ እንደቀረቡ ተደርጎ  በስብሰባ አዘጋጆች የተዘጋጁ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ፣ ሰብሳቢዎቹ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ቢውሉም መምህራኑ ግን አሁንም በዝምታ አልፈውታል።

በሶስተኛው ቀን አጠቃላይ የነበረው የተሰብሳቢ ሁኔታ ያላማራቸውና ያስመረራቸው  ሰብሳቢዎች ንዴታቸው ከሚችሉት በላይ በመሆኑ አዳራሹን በመልቀቅ ለመሄድ ተገደዋል፡፡

ዝምታ ያሸነፋቸው የህውሃት ኢህአዴግ አመራሮች ታጅበው ሲወጡና ሲገቡ ሰንብተው፣  ያለምንም ውጤት ሲሰናበቱ የባህር ዳር የኒቨርስቲ ሰራተኞችና ደስታቸውን ገልጸዋል። የገዢው ፓርቲ ሹሞች ከተሰናበቱ በሁዋላ  የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በየትምህርት ክፍሉ የተዘጋጁትን አመታዊ እቅዶች ሰምቷል፡፡እስከ መጨረሻ በዝምታው የጸናው የግቢው ማህበረሰብ ጽናቱን ይዞ በመቀጠል ያለምንም አስተያየትና ንግግር ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ሲሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞውን አጠናክረው ይቀጥላሉ በሚል ስጋት ወላጆችን ሲያነጋግር ሰንብቷል። ተማሪዎችም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ተመሳሳይ ስልጠና ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።