በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከሆሊስቲክ ፈተና ጋር በተያያዘ ተማሪዎች የጀመሩትን አድማ ተከትሎ ፖሊሶች በተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጸሙ

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከሆሊስቲክ ፈተና ጋር በተያያዘ ተማሪዎች የጀመሩትን አድማ ተከትሎ ፖሊሶች በተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጸሙ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ/ም) ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በምህንድስና ግቢ የሚማሩ ተማሪዎች የጀመሩት አድማ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የልዩ ሃይል አባላት ወደ ተማሪዎች ግቢ በመግባት ድብደባ ፈጽመዋል። አንዳንድ የተጎዱ ተማሪዎች ወደ ህክምና ጣቢያዎች ተወስደዋል።የፖሊስና መከላከያ ሃይሎች ተማሪዎችን ከግቢ ለማስወጣት በአጥር ዘለው ሲገቡ የአይን ምስክሮች የተመለከቱ ሲሆን፤አብዛኞች ተማሪዎች ዩኒቨረስቲው ግቢ አቅራቢያ ባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የግለሰብ ሆቴሎች አካባቢ በመጠለል ሁኔታውን እየተከታተሉ ነው፡፡
ተማሪዎች በአንድ ፈተና ከሃምሳ በታች ካመጣችሁ ከግቢው ትባረራላችሁ በሚል ዩኒቨርስቲው በአዲስ ያወጣውን መመሪያ በመቃዎም ወደፈተና ክፍል አንገባም በማለታቸው አመራሮች የማትፈተኑ ከሆነ ግቢውን ለቃችሁ ውጡ በሚል ልዩ ሃይል አስገብተው ለማስወጣት በተደረገው ሙከራ ግጭት መነሳቱን ወኪላችን ዘግቧል።
ከከተማ ወደ አባይ ማዶ የሚወስደው ዋናው አስፓልት ተዘጋ ሲሆን ግቢው በልዩ ሃይል ፖሊሶችና መከላከያ አባላት ተወሯል፡፡
ሰኞ ዕለት ተጀምሮ የነበረው የማጠቃለያ ፈተናም በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ተቋርጧል፡፡ተማሪዎች ከምኝታ ክፍላቸው አንዳይወጡ በመደረጋቸው አልፎ አልፎ የህብረት ጩኸት ያሰማሉ፡፡