ግንቦት ፯ ( አባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ከተማ የደረሰውን ተደጋጋሚ የቦንብ ጥቃት መንስኤና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ ባለመቻላቸው የተገመገሙት የባህርዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ውበቱ አለን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ፖሊሶች ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።
በተባረሩ አዛዦች ቦታ የሚተኩት አዲሶቹ አዛዦች፣ ነባሩ አመራር ሊደርስበት ያልቻለውን ህዋስ አጥንተው እንዲደርሱበት ልዩ ትእዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በከተማው ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞቸውን ሲገልጹ የነበሩ ወጣቶችን ወይም ለአገዛዙ ጥሩ አመለካከት የላቸውም ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በጅምላ በማፈስ እና አስጨናቂ ምርመራ በማድረግ መረጃ ለማግኘት ሙከራ እንዲያደርጉ ታዘዋል። በከተማዋ አዲስ የእስር ዘመቻ ሊጀመር እንደሚችልና ወጣቶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምንጮች አሳስበዋል።
የተቃዋሚዎችን አስተሳሰብ ያራምዳሉ ተብለው ከተገመገሙ እና ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉት የክልል የፖሊስ አመራሮች መከካል ኮማንደር ፍቅረሰላም ፣ ኮማንደር ካሴ፣ ኮማንደር ቢያዝን ማንአስብ፣ ኮማንደር ደረጃ አቻምየለህ እንዲሁም ኮማንደር አንማው አለሜ ይገኙበታል።ከእነዚህ መካከል ኮማንደር ፍቅረሰላም ሙሉ በሙሉ ከሃላፊነት ሲነሳ፣ ሌሎቹ ደረጃቸው ተቀንሶ እንዲሰሩ ተደርገዋል።
ከባህርዳር ፖሊስ መምሪያ ደግሞ የመመሪያውን ሃላፊ ኮማንደር ውበቱ አለ እና ምክትሉን ኮማንደር ጥበቡ ሃይሉን ጨምሮ ፣ የምርምራ ሃላፊው ኮማንደር እንየው ጌጡ፣ የወንጀል ምርመራ ሃላፊው ኮማንደር መኮንን አለ እንዲሁም ኮማንደር ሙሉጌታ አያልነህ ከሃላፊነት መውረድ ብቻ ሳይሆን፣ በከተማው ውስጥ የታዩቱን ፍንዳታዎች ባለመቆጣጠር እንዲሁም ኮማንድ ፖስቱ የሚሰጠውን ትእዛዝ በተለያዩ መንገዶች በመቃወም እና የተቃዋሚዎችን ሃሳብ በማራመድ ከፍተኛ ወንጀላ ተሰንዝሮባቸዋል። ግለሰቦቹ ሊከሰሱ ይችላል የሚሉ ፍንጮች መኖራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የተቋቋመው ራሱን ኮማንድ ፖስት ብሎ የሚጠራው ወታደራዊ እዝ የፖሊሶችን ስራ ጠቅልሎ በመውሰዱ ከፖሊሶች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል። አብዛኛውን ፖሊሶች ከስራ ውጭ ያደረገውና በአንድ አገር ሁለት አይነት መንግስት የመሰረተው ኮማንድ ፖስቱ፣ በሂደት አሰራሩን ይቃወማሉ ያላቸውንና ለህወሃት ጥላቻ አላቸው የተባሉ የብአዴን አባላትንና አመራሮችን እየነጠለ መምታት መጀመሩን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢህአዴግ ግምገማውን ከፖሊሶች በተጨማሪ ወደ ወታደሮች በማዞር ከህዝብ ጎን ቆመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ወታደራዊ ሀላፊዎችን ከስልጣን ለማባረር ግምገማ እንደሚጀመር ምንጮች ገልጸዋል።