ሚያዝያ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደረሰበትን ህዝባዊ ማዕቀብ መቋቋም የተነሳነው በህወሃት/ብአዴን የሚተዳደረው ዳሸን ቢራ ስሙን ባላገሩ ቢራ በሚል ቀይሮ ባህርዳር ላይ ያዘጋጀው የሙዚቃ ዝግጅት፣ ፍንዳታ መካሄዱን ተከትሎ ፖሊሶች በድንጋጤ በመተኮሳቸው የ2 ሰዎች ካለፈ በሁዋላ፣ ከፍተኛ ብስጭትና ሽንፈት የደረሰበት ገዢው ፓርቲ፣ “ይህን ያክል ጥበቃ ተመድቦ ፣ ይህን ያክል ወታደር ጥበቃ እያደረገ እንዴት ቦንብ ሊገባ ቻለ? “ በሚል የእለቱን ተረኛ አዛዦችን ጨምሮ 7 የፌደራል ፖሊሶች ታስረዋል። ከታሰሩት መካከል 2 የቆሰሉ የፌደራል ፖሊስ ጠባቂዎችም ይገኙበታል።
አንድ ኢንስፔክተር “ ተደፍረናል፣ አፍረናል” በማለት ሲናገር መደመጡን የሚገልጹት ምንጮች፣ በቅንብሩ የፖሊሶች እጅ አለበት በሚል ጥርጣሬ መያዛቸው ታውቋል።
ከሳምንት በፊት በከተማዋ ተልጥፎ የነበረው የባላገሩን ቢራ ፖስተር መቀደድ ምልክት ሊሆናቸው ነበር ሲሉ የሚናገሩት ደግሞ የባህርዳር ነዋሪዎች ናቸው። በአገዛዙ ወታደሮች ደም እንደጎርፍ በፈሰሳባት ባህርዳር ፣ የፈሰሰው የወጣቶች ደም ሳይደርቅ፣ የደሙ አፍሳሾች በእጃቸው ላይ ያለውን ደም ሳያነጹ፣ የህዝቡን ሀዘን ከምንም ባለመቁጠር የከሰረውን ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ ያደረጉት ሙከራ በባህርዳር ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ እንደነበርና፣ ፍንዳታውም የቁጣው መገለጫ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ታፍሰው የታሰሩ ቢሆንም፣ እስካሁን የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለማግኘት አለመቻላቸው መርማሪዎችን እንዲሁም መሪዎችን ፍርሃት ላይ እንደጣላቸው ምንጮች ይናገራሉ። “ባህርዳር ላይ ያልደረሰንበት ህዋስ አለ” በሚል ተጨማሪ ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል። በስራ ምክንያት አምሽተው የገቡ የባጃጅ አሽከርካሪዎች እየተያዙ 400 ብር መቀጫ ገንዘብ እየከፈሉ መሆኑን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።
ባህርዳር በነሃሴ ወር ከኦሮሞ ህዝብ ጋር አሁን ደግሞ በድጋሜ ከጎንደር ህዝብ ጋር ያለውን የትግል አንድነት አጠናክሯል የሚሉት ነዋሪዎች፣ የባህርዳር ህዝብ የጀመረውን ከዳር ሳያደርስ አንገቱን ድፈቶ የማይቀመጥ መሆኑን ይገልጻሉ።
ህዝቡ በውጥረት ውስጥም ሆኖ እንኳን በሰርግ ቦታዎች ሳይቀር አገራዊ መልእክት ያላቸውን ዜማዎችን እያዜመ ኢትዮጵያዊነቱን ከፍ አድርጎ እያሳየ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ በተለይ የቴዎድሮስ ካሳሁን አዲሱ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ይገልጻሉ።
በሰርግ ቦታዎች ላይ ርችት የሚተኩሱ ሰርገኞች ኮማንድ ፖስቱን በመጣስ በሚል ሰበብ መያዛቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በባህርዳር ማረሚያ ቤት እሳት ተነስቶ እንደነበርና ወዲያው በቁጥጥር መዋሉን መረጃዎች ደርሰውናል።