(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 4/2011) በባህርዳር ነገ ለሚካሄደው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አቀባበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ኮሚቴው አስታወቀ።
የንቅናቄው አመራሮች ዛሬ ባህርዳር መግባታቸውም ታውቋል።
ከባህርዳር በተጨማሪ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎችም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮችና አባላትን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በጎንደር የፊታችን እሁድ ተመሳሳይ የአቀባበል መርሃ ግብር እንደሚኖር አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በ32 ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል።
ቅዳሜና ዕሁድ በባህርዳርና ጎንደር ለሚደረገው የአቀባበል ዝግጅት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራርና አባላቱ ከዛሬ ጀምሮ ባህርዳር እየገቡ ነው።
የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፡ ዋና ጸሀፊው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች አመራሮች ባህርዳር መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በነገው ዕለት በባህር ዳር ስታዲየም ለሚዘጋጀው አቀባበል ፕሮግራም ከተለያዩ የዕለም ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የንቅናቄው አባላትም እስከ ማምሻውን ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባህርዳር ሳምንቱን ለአቀባበል ፕሮግራሙ ስትዘጋጅ ቆይታለች።
ከተማዋ በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማና በአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ፎቶግራፎች የደመቀች ስትሆን እንኳን ለአገራችሁ አበቃችሁ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች በተለያዩ የከተማዋ ክፎሎች ተሰቅለው ይታያሉ።
የባህርዳር የአርበኞች ግንቦት ሰባት አቀባበል ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ለሀገራቸው መስዋዕትነትን የከፈሉ የንቅናቄውን አመራሮች ለመቀበል የባህር ዳር ህዝብ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቋል።
እንግዶቻችንን ተቀብለን በሰላም እስክንሸኝ ሁሉም ወገን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን ብሏል ኮሚቴው።
በነገው ዕለት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የንቅናቄውን አመራሮች እንዲቀበልም ኮሚቴው ጥሪ አድርጓል።
በሚቀጥለው ቀን ዕሁድ በጎንደር ከተማ ተመሳሳይ የአቀባበል መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።
እነእመዋይሽ አለሙና በእስር ቤት ስቃይ የደረሰባቸው ታጋዮች በጎንደሩ የአቀባበል ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ ወታደራዊ ሰፈሩን ዘግቶ ወደ ሀገር ቤት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የገባ ሲሆን በአዲስ አበባና በሌሎች 31 ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።