በባህርዳር የተካሄደው የመጀመሪያ ቀን የስራ ማቆም አድማ ውጤታማ መሆኑን አስተባባሪዎች ገለጹ

ጥቅምት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከጥቅምት 1 እስከ 5 በተጠራው የአማራ ክልል የስራ ማቆም አድማ  በከተማዋ የሚገኙ  ሱቆች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን በሶስቱም የባህር ዳር ታላላቅ ገበያዎች ማለትም በአባይ ማዶ በቅዳሜ ገበያና በኪዳነ ምህረት ገበያዎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ

ሳያሳዩ የመጀመሪያው ቀን ተጠኗቋል፡፡ በዋናው የቅዳሜ ገበያ ውስጥ የሚገኙ የአዳራሽ ሱቆችና ልዩ ልዩ የሸቀጥ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በመዘጋት ለስራ ማቆም አድማው ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል፡፡የከተማው ኮማንድ ፖስት አንዳንድ የአዴት ተራ አካባቢ ሱቆች እንዲከፈቱ ነጋዴዎችን በማስገደድ ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጫና የበዛባቸው  የተወሰኑ ሱቆች ከሰዓት በኋላ ተከፍተው ታይተዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኙት የሞባይል ቤቶች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ነጋዴዎቹ ሱቆች መዘጋታቸው በተለይ በእሬቻ በዓል ላይ በጅምላ ለተጨፈጨፉ ወገኖችና በየእለቱ በደቡብና ኦሮሚያ በአገዛዙ  ለሚሰው ወገኖች መታሰቢያ በመሆኑ በደስታ መዝጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተወሰኑ ባጃጆች በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን አብዛኛው የባጃጅ አሽከርካሪዎች ግን በተለያዩ የግል ግቢዎች ተሸከርካሪዎችን በመደበቅና በማሳደሪያ የሚገኙትን ባጃጆች ታርጋቸውን ራሳቸው በመፍታት አድማውን መቀላቀላቸውን አሳይተዋል፡፡ ነጋዴዎች በአንድ ድምጽ ሆነው ተቃውሞውን ማድረጋቸውን የአነጋገርናቸው የከተማዋ ነጋዴዎች የገለጹ ሲሆን፣ መስተዳድሩ የንግድ ድርጅቶችን በሚዘጉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስቀድሞ የሰጠው ማስፈራሪያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል

ሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቁት አስተባባሪዎች፣ አገዛዙ ወደ ማይቀረው ሞቱ እየተጓዘ በመሆኑ ትግሉን በማጠናከር የሞቱን ሰአት ማፋጠን አለብን ብለዋል። ሌሎች የትግል ስልቶችም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

የስራ ማቆም አድማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በወጣ ማግስት መሆኑ፣ ገዢው ፓርቲ በጦር ሃይሉ ህዝባዊ ተቃውሞውን ለማፈን የሚያደርገው ሙከራ የማይሳካለት መሆኑን አመላካች ነው በማለት ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በባህርዳር ተደርጎ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ የአጋዚ ወታደሮች በርካታ ወጣቶችን መግደላቸው ይታወቃል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም ታስረው ስቃይ ደርሶባቸዋል።

ገዢው ፓርቲ የባህርዳር ተቃውሞ በርዷል በሚል የተወሰነ ሰራዊቱን ከከተማው አስወጥቶ ወደ አዲስ አበባ ወስዷል።