(ኢሳት ዜና —ነሐሴ 2/2009) በባህርዳር የተካሄደውን አድማ ተከትሎ በምሽት መብራት በማጥፋት ወጣቶች እየታፈሱ መሆናቸው ተነገረ።
የወጣቶቹ መታሰር በህዝብ ውስጥ ቁጣን ፈጥሯል።
ከአድማው መመታት በኋላ ከፓፒረስ ሆቴል ወደ ቡና ባንክ መሄጃ ማንነቱ ያልታወቀ ወጣት ተገድሎ ተገኝቷል።
በባህር ዳር የንግድ መደብሮችና ሆቴሎች ረፋዱ ላይ ተከፍተዋል።ይሁንና የአገዛዙ ባለስልጣናትና ታጣቂዎች አሁንም በስጋትና በፍርሃት ውስጥ መሆናቸው ነው የተነገረው።
አድማ በታኝ ወታደሮችና የጸጥታ ሃይሎች የርእሰ መስተዳድሩን ቢሮ ጨምሮ በፓርቲ ጽህፈት ቤቶችና በአገዛዙ ተቋማት አሁንም ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአድማው የተሳተፈው ህዝብ በርካታ ቢሆንም በመሀል ከተማ መደብሮቻቸውን የዘጉ ነጋዴዎች ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በቀበሌ 11 አባይ ማዶ ገበያ፣ቀበሌ 16ና ቀበሌ 14 የተወሰኑ ሱቆች ዝግ ሆነው መዋላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት በባህርዳሩ አድማ የአገዛዙ ካድሬዎችና የፓርቲ አባላት ተሳትፈዋል።
ይህ ሁኔታም በባለስልጣናቱ ዘንድ ግርምታን ፈጥሯል።እናም በአድማ የተሳተፉትን የስርአቱ ካድሬዎችና የፓርቲ አባላትን በመለየት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከበላይ ባለስልጣናት ትእዛዝ መውረዱ ነው የተነገረው።
በአማራ ክልል ርእሰ ከተማ ባህርዳር ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ በመኖሩ አሁንም በአካባቢው ውጥረት ነግሶ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።