ነሃሴ ፲፮ ( አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ዘጋቢያችን እንደገለጸው ሁለተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የስራ ማቆም አድማ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ተዘግተው ውለዋል፡፡ ሁሉም የግል ባንኮች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን፣ የፖስታ ቤት ባለሙያዎችም በስራ ማቆሙ አድማ ተሳታፊ በመሆን መስሪያ ቤቱን ዘግተዋል፡፡ የተለያዩ የክልል ቢሮዎች ሰራተኞቻቸው በአድማው እንዳይሳተፉና ቢሮ እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም፣ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ ‹‹ እኛም የህብረተሰቡ አንድ አካል ነን! ›› በማለት ወደ ስራ አለመሄዱን ለማወቅ ተችሎአል።
በትራንስፖርት አገልግሎት ረገድ ዛሬም እንደ ትናንቱ የሃገር አቋራጭ እና መለስተኛ አውቶቡሶች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ በትላንትናው እለት በተዘዋወሩ ሶስት ባጃጆች ላይ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት መስተዳድሩ ዛሬ የታጠቁ ፖሊሶችን የያዙ ባጃጆች በማሰማራት ቀኑን ሙሉ ሲዘዋወሩ ታይተዋል፡፡የባጃጅ አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት አንድ ፖሊስ ቀኑን ሙሉ ይዘው ለሚዞሩበት 400 ብር ይከፈላችኋል ተብለው እንደተገደዱ ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ትራንስፖርት ሰራተኞች ዛሬ በመስራት ላይ ያሉትን ባጃጆችና ታክሲዎች እንዲመዘግቡ ቢታዘዙም፣ ስራውን ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለአሽከርካሪዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በከተማው ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አራት የከተማ አውቶብሶች ብቻ ሲሆኑ፣ አብዛኛው ህብረተሰብ በቤቱ ቁጭ ብሎ ተቃውሞውን እየገለጸ ይገኛል፡፡ ተቃውሞው እስከ ረቡዕ ድረስ እንደሚቀጥል ህብረተሰቡ መግባባት ላይ መድረሱን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል፡፡
የባህርዳር ህዝብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በከተማው ታሪክ የመጀመሪያ የተባለ ሰላማዊ ሰልፍ እና የስራ ማቆም አድማ አድርጎአል። ነሃሴ አንድ ተደርጎ በነበረው ተቃውሞ ላይ የአጋዚ ወታደሮች የወሰዱት ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ የከተማው ህዝብ ስርዓቱን በቃኝ ማለቱን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።