በባህርዳር ከተማ የሚፈጸመው ሙስና ተባብሶ ቀጥሎአል።

ጥቅምት (አምስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በመስተዳድሩ ውስጥ የሚሰሩ የኢሳት ወኪሎች እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በመስተዳድሩ ውስጥ የሚፈጸመውን ሙስና ማጋለቱን ተከትሎ መንግስት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ከቦታቸው በማንሳት ወደ ሌሎች መስሪያ ቤቶች በማዛወር የህዝቡን ቅሬታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም፣ አሁንም በአስተዳደሩ ኢንዱስትሪ ልማትና ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ስር በሚገኙት የከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ፣ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረት ምዝገባ ሂደት እንዲሁም የልማታዊ ባለሀብት መሳብና መደገፍ ስራ ሂደት ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ምዝበራ እየተፈጸመ ነው።

ባለሀብቶች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ ፕሮጀክታቸውን ይዘው ሲመጡ በደላሎች አደራዳሪነት እስከ 100 ሺ ብር እንደሚከፍሉ ሰራተኞች ገልጸዋል።

የስመ ንብረት ዝውውር በሚባለው ክፍል ደግሞ ግለሰቦች ቤታቸውን ሽጠው ስም ለማዛወር ከ10  እስከ 30 ሺ  ብር ጉቦ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ጉቦ የሚከፍሉ ሰዎች ቤታቸው ዝቅ ብሎ ስለሚገመትላቸው የሚከፍሉት ግብርም ይቀንሳል።

የከተማ አስተዳደሩ ሴከትር ከመስከረም 18፣ 2006 ጀምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት ባካሄደው የአመራርና ስራ ሂደት የመሪዎች ውይይት ወቅት ወርቅነህ ደመቀ፣ አየነው አለሙ፣ ገብሩ ጸሀይነህ፣ ፋሲል እና ፍቅር ስማቸው በኪራይ ሰብሳቢነት ተነስቷል። አየነው አለሙ የከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት የስራ ሂደት መሪ፣ አቶ ገብሩ ጸሀይ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንበረት ምዝገባ ስራ ሂደት መሪ እንዲሁም አቶ ወርቅነህ ደመቀ የልማታዊ ባለሀብት መሳብና መደገፍ የስራ ሂደት መሪ ናቸው።

አቶ ገብሩና አቶ አየነህ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ክስ ቢያቀርብባቸውም ክሱ ተቋርጧል።

የባህርዳር ከተማ ማህበራት ተጠሪ ጽህፈት ቤትም ቤት ተመዝጋቢዎችን ከ3000 እስከ 10 ሺ ብር በህገወጥ መልኩ እያስከፈለ እንደሚገኝ ወኪሎቻችን ገልጸዋል።

ባለፈው አመት እነዚህ ወኪሎች የላኩትን መረጃ ተከትሎ በቀረበው ዘገባ መንግስት ከንቲባውን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናትም ከስልጣን እንዲወርዱ አድርጓል ። ይሁን እንጅ ግለሰቦቹ በሌሎች መስሪያ ቤቶች በሀላፊነት እንዲመደቡ ተደርጓል።