ሰኔ ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰኔ 22 ከሌሊቱ በ6፡00ሰዓት በባህርዳር ከተማ ትልቁ ገበያ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ የጎማ መደብሮች፣የቤት ዕቃ መሸጫዎች የባልትና ውጤት አቅራቢዎችና በርካታ የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡
የአካበቢው ህብረተሰብ የአሁኑ ቃጠሎ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ የገበያ ቦታዎችን አስለቅቆ ለባለሃብቱ ለመስጠት ሲደረግ የነበረው ሴራ አንድ አካል ነው ይላሉ ፡፡
ከአመታት በፊት በደሮ ተራ አካባቢ የነበሩ ነጋዴዎችን ለማስለቀቅ ሞክሮ አልሳካልህ ያለው መንግስት፣ አካባቢውን በእሳት በመለኮስ ቦታውን ለዳሸን ባንክ መስሪያነት ማጠሩን የሚያወሱት ተጎጂዎች ፣ አሁንም ቦታው ለባለሃብት ተፈልጎ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተፈጸመ መሆኑን በምሬት ይገልጻሉ።
ቦታው ላይ መልሰው በመስራት የወደመባቸውን ንብረት እንዲመልሱ የመንግስት እገዛ ካልተደረገ ከፍተኛ ታቃውሞ ለማሰማት መዘጋጀታቸው ተጎጂዎች ተናግረዋል፡፡
እሳቱ እስከ 23/10/08 ከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ የቆየ ሲሆን ፣ በቃጠሎው በአስር ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ተጎጂዎች ተናግረዋል፡፡
የመንግስት አካላት ቦታዎችን ሲፈልጉ በሰላማዊ መንገድ ማስለቀቅ ሲችሉ እንዲህ አይነት ጥፋት በተደጋጋሚ መፈጸማቸው እንዳሳዘናቸው የባህርዳር ነዋሪዎች ለሪፖርተራችን አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡