በባህርዳር እና በዙሪያዋ ወረዳዎች ተይዘው ከታሰሩት መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ፍድር ቤት ሳይቀርቡ ለወራት መታሰራቸው ታወቀ

ታኅሣሥ ፲፯ (አሥራ ሠባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከነሃሴ ፣ 2008 ዓም ጀምሮ በባህርዳር ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች ማለትም በባህርዳር ዙሪያ፣ ጎንጂ ቆለላ፣ ይልማና ዴንሳ፣ ሜጫ፣ አቸፈር፣ ባህርዳርና ደራ ወረዳዎች ተይዘው ከታሰሩ ከ4 ሺ በላይ ወጣቶች መካከል 1 ሺ 500 የሚሆኑት እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በባህርዳር ወህኒ ቤት ታስረው ለስቃይ እየተዳረጉ ነው።

እስረኞቹ በከፍተኛ የውሃ እና ህክምና ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን የገለጸው ወኪላችን፣ የቧንቧ ውሃ ማዳረስ ስላልተቻለ፣ በቦቴ እየመጣና ማጠራቀሚያ ላይ እየተገለበጠ እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።

በሌላ በኩል ቀደም ብለው በወልዲያና አካባቢዋ ባሉ ከተሞች ታፍሰው ከ 1 እስከ 3 ወር ታስረው የተለቀቁ ከ60 በላይ ዜጎች ተሃድሶ ሳይወስዱ ተለቀዋል በሚል እንደገና ሊታሰሩ መሆኑ ታውቋል። አንዳንድ አስቀድሞ መረጃው የደረሳቸው ወጣቶች ፣ ከአካባቢው ተሰውረዋል።

በቅርቡ የተለቀቁት ወደ 10 ሺ የሚጠጉ እስረኞች የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ትምህርት ተምረው መመረቃቸው በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ሲነገር ሰንብቷል።

ቀደም ብሎ “ተሃድሶ” ሳይሰጣቸው የተፈቱትን መልሶ ለማሰር የሚደረገው እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።