(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 12/2010) በባህርዳር ከተማ ነዋሪዎችን የማዋከብና የእስር ርምጃ ከቀን ቀን እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ።
ካለፉት 2 ቀናት ጀምሮ በተከታታይ በየመንገዱ በቀን ጨምሮ እየታፈኑ የሚታሰሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በጣና ፎረም ስብሰባ ላይ ይገኛሉ መባሉን ተከትሎ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይገኙበታል የተባሉ የሰሞኑ ስብሰባዎች መነሻ በማድረግ በባህርዳር ከተማ በየመንገዱ ከፍተኛ የሚባሉ ፍተሻዎች እየተካሄዱ ነው።
በተለይ ምሽት ላይ ከእግረኛ እስከ ተሽከርካሪ ድረስ ከፍተኛ ፍተሻዎች በክልሉ ልዩ ሃይል አድማ በታኝ ፖሊሶች እ እንዲሁም በፌድራል ፖሊስ አማካኝነት እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በባህርዳር ከተማ ከገበያ ወደ ቴክስታይል መስመር እና ፔዳ በሚወስደው ዋና መስመር ትናንት ምሽት ከምርመራ ጥያቄዎች ጋር ለሰዓታት በማስቆም የነበረው ፍተሻ በአይነቱ የተለየ እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
ወደየት እየሄድክ ነው ? ምን ልታደርግ ? ቤትህ የት ነው ? ስልክ ቁጥርህ ? የሚሉ ያልተለመዱ ጥያቄዎችም ይጠየቃሉ ተብሏል።
የተወሰኑ ባጃጆችን ደግሞ የማታ ፍቃድ የላችሁም በማለት ገና ከምሽቱ በ1፡40 ደቂቃ ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ለ1 ሰዓት ያክል አግተዋቸው ነበር።
ማንኛውም ባጃጅ ግን እስከ 3 ሰዓት የሌሊት ፈቃድ ከሌለው መስራት ይችላል።
ከጊዩርጊስ ፌርማታ ወደ ሆስፒታል እና ገጠር መንገድ ኤርፖርት መስመር የሚወስደው ዋና መንገድ ጥብቅ ፍተሻ በቀንና በማታ እየተደረገበት ይገኛል።
በግምት በየ100 ሜትሩ የታጠቁ የፌደራል ፖሊሶች ቁመው ይታያሉ።
ሌላው ጥብቅ ፍተሻ ያለበት ከገበያ ወደ ቀበሌ 14 ጎጃም መውጫ ከተባባሩት ማደያ ጀምሮ ነው።
በጉዶ ባህር አካባቢ ሚኒሻዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቁመው ይታያሉ።
እንደዚሁም ከጊዩርጊስ ወደ አባይ ማዶ ያለው መንገድ በታጠቁ የፌደራል ፖሊስ እና ልዩ ሃይል አድማ በታኝ ፖሊሶች የተወረረ እና ህዝቡን በብዛት ፍተሻ እና ማዋከብ የሚፈፀምበት መንገድ ሆኗል።
በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች እየተደረገ ያለው ፍተሻና ማዋከብ እንዲሁም ድብደባና እስር ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያስመረረ መሆኑ ተነግሯል።