ሚያዚያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳሬዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አለው፤ በታሪካዊነቱ ብቻ ሳይሆን ፣ በጣፋጭነቱም ይታወቃል፡፡ በ1962 ዓም የተቁዋቁዋመው እና ለ50 አመታት ተወዳጅነቱን ጠብቆ የዘለቀው የመጀመሪያው ዳቦ ቤት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል፡
ዳቦ ቤቱን የመሰረቱት ሃጅ አድጎይ መሃመድ ወይም በከተማው ህዝብ አጣራር አባ አድጎይ ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ ቤተሰቦቻቸው ግን ድርጅቱን ይዘው በመዝለቅ እስካሁን ድረስ የከተማውን ህዝብ ዳቦ እየጋገሩ ይመግባሉ፡፡ የከተማው መስተዳደር ታዲያ፣ ሰሞኑን ድርጅቱ ያለበትን ቦታ የስርዓቱ ባለውለታ ነው ለሚባል ሰው ለመስጠት በማሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን አስቆጥቶአል፡፡
የከተማው ህዝብ ባለውለታ የሆነውን ዳቦ ቤት እንታደግ በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች የክልሉን ባለስልጣት ለመጠየቅ ፊርማ በማሰባበሰብ ላይ ናቸው፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግንባታ ካስፈለገም ቅድሚያ ለቤተሰቦቹ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ቤተሰቦቹ በቦታው ላይ መንግስት የሚፈልገውን ግንባታ ለመገንባት አቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
መንግስት በተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ ስብሰባዎች የሚነሱትን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአስቸኩዋይ እመልሳለሁ እያለ ፣ በሌላ በኩል ድሆችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ቦታቸውን ለዘመኑ ባለሃብቶች መስጠቱን ቀጥሎበታል በማለት ነዋሪዎች ትችት እያቀረቡ ነው፡