በባህርዳር ቤተክርስቲያን ተፈናቃዮችን ከግቢዋ እንድታስወጣ ብትጠየቀም አሻፈረኝ አለች

በባህርዳር ቤተክርስቲያን ተፈናቃዮችን ከግቢዋ እንድታስወጣ ብትጠየቀም አሻፈረኝ አለች
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮምያ ክልሎች ተፈናቅለው ባህርዳር በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የደህንነት አባላት ለቤተክርስቲያኗ ትእዛዝ ቢሰጡም፣ ቤተክርስቲያኗ ግን ተፈናቃዮችን ለማስወጣት ፈቃዳኛ አለመሆኗን ገልጻለች።
የደህንነት ሰራተኞች የተፈናቃዮችን አመራሮች ይዘው በማሰር እና ተፈናቃዮች ወደ መጡበት ክልል ወይም ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንዲሄዱ እንዲያግባቡ ቃል አስገብተው ከእስር የፈቱዋቸው ቢሆንም፣ ተፈናቃዮች ጥያቄያችን መልስ ሳያገኝ ወደ መጣንበት አካባቢ ለመመለስ አንችልም ብለዋል። ወደ ትውልድ ቀያችን ብንሄድም የምናርሰው መሬት አናገኝም የሚሉት ተፈናቃዮች የክልሉ መንግስት ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል። የደህንነት አባላት ከ350 ያላነሱት አፍሰው በመጫን ወደ አልታወቀ ስፍራ ወስደዋቸዋል። በአሁኑ ሰአት በቤተክርስቲያኑ ተጠልለው የሚገኙት ከ200 አይበልጡም።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ለአማራ ክልል ቴሌቪዠን በሰጠው መልስ፣ አማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውን እንደማያውቅ ገልጿል። ተፈናቃዮች በበኩላቸው የደረሰባቸውን ችግር በተደጋጋሚ በጽሁፍ ለወረዳው ባለስልጣናት ሲያስታውቁ ቢቆይም መልስ በመጣታቸውና ግድያው እየጨመረ በመሄዱ መፈናቀላቸውን ይናገራሉ። በ2010 ዓም 13 ሰዎች መገደላቸውን የሚገልጹት ተፈናቃዮች፣ የሞቱት ሰዎች እንኳ በስነስርዓት እንደማይቀበሩ ገልጸዋል።
ባለፉት አመታት ቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች የክልሉ ባለስልጣናት በሚያደርሱባቸው ተጽዕኖ የተነሳ ለግድያ፣ ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል።