ኢሳት (ጥቅምት 2 ፥ 2009)
በባህርዳር ከተማ የጸጥታ ቁጥጥር በማድረግ ላይ በነበሩ የአጋዚ ወታደሮች ላይ ሰኞ ምሽት በተፈጸመ የእጅ ቦንብ ጥቃት ሁለት አባላት መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት ገለጹ።
ወታደሮቹ በከተማዋ ቀበሌ 05 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተሽከርካሪ በመዘዋወር ላይ እንዳሉ የእጅ ቦንብ እንደተወረወረባቸውና ከሞቱን ሁለቱ ወታደሮች በተጨማሪ የተጎዱ መኖራቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች አስረድተዋል።
የፍትህና የነጻነት ሃይሎች በሚባሉ አካላት ተፈጽሟል የተባለውን ይህንኑ ጥቃት ተከትሎ በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች በአካባቢው በወሰዱት ዕርምጃ በርካታ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውም ታውቋል።
የአድማ በታኝ ወታደሮች በወቅቱ ከአጋዜ ወታደሮች ጋር በሌላ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ የነበሩ ሲሆን ጥቃቱ የአጋዚ ወታደሮችን አልሞ የተፈጸመ ነው ሲሉ ድርጊቱን ለዜና ክፍላችን ያስረዱት እማኞች ተናገረዋል።
በተያዘው ሳምንት ባህርዳር ከተማ በስራ ማቆም አድማ ውስጥ መሆኗን ያስታወቁት ነዋሪዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የንግድ ተቋማት በግዳጅ እንዲከፈቱ እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣ ማስነሳቱም ታውቋል።
ይሁንና ሰኞ ምሽት በአጋዚ ወታውደሮች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከዚሁ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።
መንግስት ከቅዳሜ ጀምሮ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን ተከትሎ በአማራ ክልል ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ሊካሄድ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል ከሃምሌ ወር ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ትጥቅ ለማስፈታት ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ አለመቻሉን ነዋሪዎች ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
ይሁንና ከቀናት በፊት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ዕርምጃውን በተጠናከረ ሁኔታ ሊካሄድ መታቀዱን የጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ለኢሳት አስታወቀዋል።
ማክሰኞ ምሽት በባህር ዳር ከተማ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ በአርማጭሆ ወረዳ በተመሳሳይ ድርጊት አንድ የፌዴራል ፖሊስ መገደሉን ሰኞ መዘገባችን ይታወሳል።