ሰኔ ፲፫( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ የተደረገውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ በመከላከያ ውስጥ በተደረገው የ “ ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ” ሰበብ ከ50 ያላነሱ እስከ ኮሎኔልነት የሚደርስ ወታደራዊ ማእረግ ያላቸውና ተራ ወታደሮችና ለስርዓቱም ታማኞች አይደሉም በሚል ታስረው እንደሚገኙ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
እስረኞቹ ጃዊ ውስጥ በሚገኝ የመከላከያ ካምፕ ውስጥ ለወራት ታስረው ከቆዩ በሁዋላ፣ በአማራነታቸው ብቻ ተገምግመው መታሰራቸውን በመግለጽ ወደ ባህርዳር ማረሚያ ቤት ተዛውረው እንዲታሰሩ ለብአዴን ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፈው ነበር። የብአዴን ሃላፊዎች ከኮማንድ ፖስቱ ጋር ባደረጉት ስምምነት ወታደሮቹ ወደ ባህርዳር ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ መደረጉን የሚገልጹት ምንጮች፣ የኮማንድ ፖስቱ መሪዎች፣ “ወታደሮቹ ከእስር ቤት እንደማያመልጡ፣ እስረኛውን ለአመጽ እንደማያነሳሱ” ብአዴን ዋስትና ይሰጠን ብለው የጠየቁ ሲሆን፣ ብአዴንም ለኮማንድ ፖስቱ ዋስትና በመስጠት ወታደሮቹ ተዛውረው እንዲታሰሩ አድርጓል።
ከ3 ቀናት በፊት፣ “የብአዴን አንዳንድ ሰዎች ለወታደሮቹ የጦር መሳሪያ አስገብተውላቸዋል” የሚል መረጃ ደርሶኛል በሚል ሰበብ የማረሚያ ቤቱ ኮማንድ ፖስት እስረኞችን በሌሊት ቤታቸውን የፈተሹ ቢሆንም ምንም የጦር መሳሪያ አልተገኘም። ትናንት ሰኞ የማረሚያ ቤቱ እስረኞ ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ በወታደሮች ግፊት የተደረገ ነው በሚል፣ የኮማንድ ፖስት አባላት ጥርጣሬያቸውን በወታደሮች ላይ ማሳረፋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ከ4 ያላነሱ በኮሎኔልነት ደረጃ ያሉ መኮንኖች በእስር ቤቱ የሚገኙ ሲሆን፣ ከ40 በላይ የሚሆኑት ወታደሮች ከተራ ወታደር እስከ መካከለኛ ሹመት ያላቸው ናቸው ብለዋል። አብዛኞቹ ወታደሮች በሰሜን ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም አካባቢ የህዝቡን አመጽ እንዲቆጣጠሩ ተልከው የነበሩና በህዝብ ላይ ለመተኮስ ፈቃድ ያለሳዩ ናቸው የሚሉት ምንጮች፣ በጃዊ እስር ቤት በቆዩባቸው ጊዜ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል።
የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ ወታደሮች ከህዝባዊ ለውጡ በስተጀርባ አሉበት በሚል አሁንም ድረስ በአይነ ቁራኛ እየታዩ ነው።
ኮማንድ ፖስቱ “የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ ፈርሷል” ብሎ እንደሚያምን የሚናገሩት ምንጮች፣ የክልሉ ፖሊሶች፣ የጸጥታና የደህንነት ሃይሎች በህወሃት የበላይነት ከሚዘወረው ኮማንድ ፖስት ጋር ለመተባበር ፈቃደኝነት አለመሆናቸው አንዳንዶች ከስራ እንዲቀነሱ ሌሎች ደግሞ እንዲባረሩ አድርጎቸዋል።
ከአዲስ አበባ የተላኩ የኮማንድ ፖስት አባላት የክልሉን የጸጥታ ሃላፊዎች ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ፣ “ክልሉ ሰው አልቧ ሆኗል፣ የጸጥታ መዋቅሩም ፈርሷል ፣ በስንት የሰው ሃይል ሲጠበቅ በነበረው ባዛር ላይ ቦንብ መወርወሩ የጸጥታ ሃይሉ መፍረሱን ነው የሚያሳያው” በማለት የተናገሩዋቸው ሲሆን፣ አብዛኞቻችሁ የትምክህት ሃይሉ ሰለባ ሆናችሁዋል ተብለው ተወቅሰዋል። ይህን ተከትሎ ሹም ሽር የተደረገ ቢሆንም፣ ኮማንድ ፖስቱ አሁንም በክልሉ ተወላጅ የጸጥታ አባላት ላይ እምነት መጣል አልቻለም።
በብአዴን በኩል ደግሞ በአሁኑ ሰአት ድርጅቱ ሁለት አይነት መልክ እንዳለው የሚገልጹት ምንጮች፣ አንደኛው ወገን “ህወሃት አብቅቶለታል፣ ጊዜው የብአዴን ነው” በማለት የህወሃትን ትዕዛዝ እንደቀድሞው ለማስፈጸም ፍላጎት አያሳይም። ከነባር አመራሮች መካከል አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ አለምነው መኮንን በቀድሞው ግንኙነት መቀጠሉ ለብአዴን ይጠቅማል የሚል አቋም እንዳላቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል። “ህወሃት ተዳክሟል፣ ከእንግዲህ ክልላችንም ህዝባችንም እንደሁለተኛ ዜጋ መቆጠሩ አብቅቷል” የሚል አቋም የሚያራምደው አንደኛው ወገን፣ ህወሃት ጉልበት ቢኖረው ኖሮ፣ በክልሉ ፕሬዚዳንት ላይ ያሳላፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ያደርገው ነበር ይላሉ። ህወሃት ከመለስ ሞት በሁዋላ መዳከሙን፣ በብአዴን ውስጥ የመለስ ትእዛዝ አስፈጻሚ ተደርገው የሚቆጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አዲሱ ለገሰ በክልሉ ውስጥ እንደ ልባቸው የሚያዝዙበት ሁኔታ መጥፋቱን በእነ አቶ አለምነው በኩል ደግሞ ህወሃት አሁንም ወታደራዊና ደህንነቱን ተቆጣጥሮ የሚገኝ በመሆኑ፣ ከህወሃት ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ለብአዴን ህልውና አደገኛ ነው በማለት የቀድሞው ግንኙነት እንዲቀጥል እየጣሩ ነው።
ህወሃት በበኩሉ ብአዴን ጥልቅ ተሃድሶ በሚል ወደ ላይ ያወጣቸው ወጣቶች የፌስቡክ፣ የአርበኞች ግንቦት 7ትና የኢሳት አይዶሎጂ የሰፈነባቸው ናቸው በሚል በብአዴን ላይ ትችቱን እያወረደ ነው።
የብአዴን አንደኛው ክንፍ የእነ አለምነውንና የእነ ደመቀን ክንፍ አሸንፎ የሚወጣ ከሆነ ህወሃት እንደ ኢህአዴግም እንደ ህወሃትም እየሆነ ፖለቲካውን ብቻውን መቆጣጠሩ ሊያከትም ይችላል በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡት ምንጮች፣ የእነ አለምነውና ደመቀ ክንፍ አሸንፎ ከወጣ ግን ህወሃት እንደ ቀድሞው የበላይነቱን ይዞ ይጓዛል ይላሉ።
በብአዴን ውስጥ ለተፈጠረው መከፋፈል ህዝባዊ አመጹና ጥልቅ ተሃድሶው አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለያዩ ዞኖች በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ህዝቡ የብአዴን መሪዎችን “አስጠቃችሁን፣ አዋረዳችሁን” በማለት ከፍተኛ ወቀሳ ያቀረበባቸው ሲሆን ፣ አብዛኞቹ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አመራሮች በህዝቡ የቀረበውን ወቀሳ ተቀብለው በበላይ አመራሩ ላይ ጫና ማሳደር መጀመራቸው በብአዴን ውስጥ እንዲሁም በብአዴንና በህወሃት መካከል ለተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ሆኗል።
በሌላ በኩል ደግሞ በባህርዳር አባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውንና በቅርቡ የተገነባውን ኮቢል የተሰኘውን የነዳጅ ማደያ ለማቃጠል ሙከራ አድርገዋል የተባሉ ወጣቶች ተይዘው ምርምራ እየተካሄደባቸው ነው።