መስከረም ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሲደረግ የነበረው የመምህራን ስብሰባ እንዲቋረጥ የተደረገው መምህራን ተቃውሞአቸውን በዝምታ መግለጻቸውን ተከትሎ ነው። ስብሰባውን የሚመሩት የአማራ ክልል ም/ሬዝዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ለተስብሳቢው ችግራችን ስር የሰደደነው ለውጥ እናደርጋለን ከአባላት ውጭ ያሉትን ሁሉ እንሾማለን ፤ አባል እናጠራለን ቢሉም ሰሚአጥተው፤ ከግማሽ ቀን በላይ በተደረገው የዝምታ አድማ በቀረቡት ሰነዶች ላይ የሚፈለገው ተናጋሪ በመታጣቱ ምክንያት ኢህአዴግ ያለመውን ግብ ሳይመታ ስብሰባው እንዲበተን አድርጓል።
ስብሰባው በ3ቱ ዋና ዋና ካምፓሶች ማለትም በፖሊ፣ፔዳ እና ዘንዘልማ እየተካሄደ ቢሆንም ከዩንቨርስቲው ማህበረሰብ ምንም አይነት የጥያቄም ሆነ የመልስ ድምፅ ሊመጣ አለመቻሉን ተከትሎ በፖሊ የነበረውን ስብሰባ ሲመሩት የነበሩት የዩንቨርስቲው ቦርድ አባል ፣የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባል እና የክልሉ ግብርና መካናይዜሽን ከፍተኛ ባለስለጣን የሆኑት ዶክተር ተሾመ በህይወቴ እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም በማለት በተሰበሳቢዎች መደንገጣቸውን ተናግረዋል።
መምህራኑ ሀገር በፈረሰበት ፣ሰብዓዊ መብት በተጣሰበት በአሁኑ እና ሞት በረከሰበት ስአት የዩኒቨርስቲ መፍረስ ወይም አለመፍረስ ፋይዳው የት ላይ ነው የሚል የዝምታ ጩኸት አስተጋብተዋል።
በፔዳ ግቢ ስብሰባውን ሲመሩት የነበሩት ዶክተር ማተቤና የብአዴኑ አቶ አለምነው መኮነንም ተመሳሳይ ያልተጠየቁ ጥያቄዎችን እንደተጠየቁ አድርገው በማቅርብ ከሰኞ 9:30 ጀምረው በራሳቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ውለዋል። የብአዴን የማእከላዊ ኮሚቴ ከፍተኛ
ባለስልጣንና የባህር ዳር ዩንቨርስቲ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አለምነው መኮነን ከወልቃይት የድንበር አከላለልን በተመለከተ ተጠየቀ ላሉት ጥያቄ መለስ ሲሰጡ “የክልሎችን ደምበር አከላለል የሚያጣቅስ የታሪክ ፖለቲካዊ ካርታ የለም” በማለታቸው የፔዳ ሙህራንን በጣም አሳዝነዋል። አብዛኛዎቹ መምህራን በተዘጋጀላቸው የምሳ ግበዣ ተካፋይ አለመሆንን መርጠዋል ።
በአሁኑ ሰዓት በመላው አማራ እና ኦሮምያ አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የግጭት ምንጭ ይሆናሉ ተብሎ በመታሰቡ ኢህአዴግ ለሰራተኞች እና ለመምህራን ምግብ እና ተጨማሪ ወጭዎችን እየሸፈነ ለማወያየት ቢሞክርም ፣ በወሎ ፣ በባህርዳር ፤ በደብረማርቆስ እና በደብረታቦር ያለው ሁኔታ ስጋት እንደጣለው አጠቃላይ የግምገማ ሰነዱ በግብረመልስ በተቀመረው የውሎ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡
በባለፉት ሃያ አምስት አመታት የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የክራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣የትምክህትና ጠባብነት አደጋዎች እንደዚሁም ሃይማኖትን ሽፋን የሚያደርገው አክራርነት ፈተናዎች አሁንም ቅርፃቸውን ቀይረው ወይም በሌላ ተተክተዉ ስላሉ ፈተናዎችን ለማለፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እዲያገዙኝ ሲል ቢጠይቅም የሚያግዘው አላገኘም።
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ደግሞ መምህራን በስርዓቱ ተስፋ መቁረጣቸውን በግልጽና በድፍረት ስብሰባውን ለሚመሩት ሬድዋን ሁሴን ነግረዋቸዋል።