ጳጉሜ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባህርዳር ከተናሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር በተያያዘ ከታሰሩት ከ1 ሺ 500 ያላነሱ ወጣቶች መካከል 600 የሚሆኑት ዛሬ ወደ ብር ሸለቆ ወታደራዊ ካምፕ የተወሰዱ ሲሆን እስረኞቹ በቆይታቸው ከፍተኛ ስቃይ እንደደረሰባቸው የአይን እማኞች ገልጸዋል። አብዛኞቹ ወጣት እስረኞች በደረሰባቸው ድብደባ የተነሳ ተጎሳቁለዋል፣ የጤና እክል ያጋጠማቸውም ቁጥራቸው በርካታ ነው። ድብደባውን መቋቋም የተሳናቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ወጣቶች በእስር ቤት ውስጥ መቀበራቸውንም የአይን እማኞች አክለው ገልጸዋል።
በፍኖተሰላም ከተማም እንዲሁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ብርሸለቆ ተወስደዋል።
በተያያዘ ዜና የህልውና አደጋ ተደቅኖብናል ያለው ኢህአዴግ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የቀድሞ ጦር አባላትን ባለፈው ሰኞ ባህርዳር ላይ በመሰብሰብ ድርጅታቸውን እንዲያድኑ ጥሪ አቅርቧል። አባላቱ ግን “ እስከዛሬ ረስታችሁን ስታበቁ አሁን ሲጨንቃችሁ ነው ወይ ወደኛ የምትመጡት” በማለት መልስ እንደሰጡዋቸው፣ ከተሳታፊዎች መካከል አንዱ ለኢሳት ተናግሯል።
ኢህአዴግ የድርጅቱን አባላት በእየቦታው በመሰብሰብ ፣ ድርጅቱን ከአደጋ ታደጉት እያለ በመማጸንና በማስፈራራት ላይ ነው።
በክልሉ ውስጥ አሁንም በርካታ የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል። በደብረታቦር በርካታ የስጋ ቤቶችና ሆቴሎች የተዘጉ ሲሆን፣ ነጋዴዎች ከንግዲህ በአድማ አንሳተፍም ብላችሁ ፈርሙ ቢባሉም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሆቴሎቹና ስጋ ቤቶች አሁንም ድረስ እንደታሸጉ መቀጠላቸውን ነጋዴዎች ገልጸዋል።