ኢሳት (መስከረም 23: 2009)
ሰኞ ረፋድ ድረስ ተጨማሪ 23 አስከሬን በእሬቻ በዓል አከባበር ስፍራ በነበረ ጉድጓድ ውስጥ መውታጣቸውን እማኞች ለዜና ክፍላችን አስታውቀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የበዓሉ ታዳሚዎች ዕሁድ ምሽት ጀምሮ የሞቹ ሰዎችን ለማፈላለግ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ በአጠቃላይ ተጨማሪ የ26 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ገልጸዋል።
መንግስት ድርጊቱን ለመሰፋፈን ጥረት በማድረግ ላይ በመሆኑ እማኝነታችንን መስጠት እንፈልጋለን ያሉት ግለሰቦች በስፍራው የነበረው ጉድጓድ በአግባቡ አለመታጠሩና አለመጠናቀቁ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አክለው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልልና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ለእንግዶች ማረፊያ ሲባል ግንባታ መከናወኑን ቢገልፅም በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ህጻናትን እናቶችን ከሟቾች መካከል የሚገኙበት ሲሆን፣ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር በአግባቡ ለመናገር አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አርብ ባስተላለፈው መልዕክት የእሬቻ በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ለማድረግ ከፍተኛ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል ሲል መገልፁ ይታወሳል። የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የፌዴራል የጸጥታ አባላት ከረቡዕ ጀምሮ ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ መሆኑን ለኢሳት ሲገልጽ ቆይተዋል።
በዕሁድ የእሬቻ በዓል አከባባር ላይ የታደሙ ዕማኞች የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ መክፈታቸውንና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሰጡት ማስተባበያ ሃዘን እንደገለጸባቸው አከለው አስረድተዋል።