በቡኖ በደሌ የማፈናቀል ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 14/2010) በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ገቺና ዲዴሳ ወረዳዎች በህወሀት መንግስት የተቀነባበረ የማፈናቀል ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ከደርግ መንግስት የስልጣን ዘመን ጀምሮ በአካባቢው የሰፈሩና በአብዛኛው ከአማራ የመጡ ኢትዮጵያውያን ሆን ተብሎ ለዘመናት ከሚኖሩበት ቦታ እንዲለቁ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ በምዕራብ ሀረርጌ ዳሮ ለቡ ወረዳ የሶማሌ ልዩ ሃይልና የአጋዚ ሰራዊት በጋራ ህዝቡን እያሸበሩት መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ አንድ አባል ተገደሎብኛል ሲልም አስታውቋል።

ፋይል

ቡኖ በደሌ አሁንም ተነስቷል። ባለፈው የአማራ ተወላጆች የሆኑ ነባር የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በህወሀት መንግስት የተቀነባበረ የማፈናቀል ርምጃ ተወስዶ ነበር።

በህዝብ ተቃውሞ ምክንያት ርምጃው ቆሞ የተፈናቀሉትም ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።

የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት በኢትዮጵያውያን መሃል ግጭት በመፍጠር የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የሚንቀሳቀሰው የህወሃት አገዛዝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መሰል የእርስ በእርስ ግጭት መለኮሱን በመቀጠል በቡኖ በደሌ ዞን ሁለት ወረዳዎች ሰሞኑንም የማፈናቀል ርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በህወሃት አገዛዝ ስውር ተልዕኮ የተሰጣቸው አንዳንድ የአካባቢው የመንግስት ሹመኞች በተለይ የአማራ ተወላጅ በሆኑ ነዋሪዎች ላይ ስልታዊ የማፈናቀል ርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው።

በገቺና ዲዴሳ ወረዳዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ንብረታቸውን ሸጠው ከአካባቢው እንዲለቁ ስውር በሆነ ስልት ዘመቻ መከፈቱን ለማወቅ ተችሏል።

የአማራና የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን በህወሃት አገዛዝ የተቀነባበረውን ሴራ እያመከኑ፣ አንድነታቸውን ይበልጥ እያጠናከሩ መሆናቸው ያላስደሰተው አገዛዙ ከዚህም የከፋ የተንኮል ርምጃ ሊወሰድ ስለሚችል ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከአካባቢው ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።

በሌላ በኩል ዛሬ ጠዋት በምዕራብ ሀረርጌ ዳሮ ለቡ ወረዳ የሶማሌ ልዩ ሃይል ከአጋዚ ሰራዊት ጋር በመሆን ህብረተሰቡን እያሸበሩት መሆኑን ከስፍራው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የነዋሪውን እንቅስቃሴ በመገደብ የስነልቦና ሽብር የፈጠሩት የልዩ ሃይሉና የአጋዚ ሰራዊት አባላት በአንዳንዶቹ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውም ታውቋል።

ህዝቡ የአጸፋ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን የከፋ አደጋ ሊፈጸም እንደሚችልም ተገልጿል።

ከቅትር በኋላ ስላለው ሁኔታ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ኦፌኮ አንድ የወረዳ የአመራር አባሉ መገደሉን አስታውቋል።

በቄለም ወለጋ የፓርቲው የምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩትና የሁለት ልጆች አባት አቶ ተመስጌን ሳፎ ተገድለው መገኘታቸውን የጠቀሰው ኦፌኮ የግድያውን ሁኔታ እያጣራሁ ነው ብሏል።

በርካታ አባላቱ ከስራ እንደሚፈናቀሉበትም አስታውቋል። ፓርቲው በቅርቡ እንደገለጸውም አባላቱ የትምህርትና የስራ እድል ይነፈጋሉ። ብድርና እርዳታ እንዳያገኙም ይደረጋል።