ታህሳስ ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ወታደራዊ ምንጮች እንደገለጹት ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት በሰራዊቱ መካከል የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ በርካታ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ከሆኑ በሁዋላ ባለፈው ሀሙስ ከመቀሌ እ ከአፍዴራ የተንቀሳቀሱ ወታደራዊ አዛዦች በግጭቱ የተሳተፉት ሁሉ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ማድረጋቸው ታውቋል። በእለቱ ከፍተኛ ግምገማ መካሄዱንም ለማወቅ ተችሎአል።
በአሁኑ ሰአት አንጻራዊ ሰላም መስፈሩን በአካባቢው የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች ለኢሳት ገልጸዋል።
በቡሬ ግንባር በሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ማንዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ማክሰኞ ሌሊት የእርስ በርስ ግጭት ተፈጥሮ እንደነበርና ቁጥሩ ከ12 እሰከ 40 የሚደረስ የሰራዊት አባለት መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። 15 ወታደሮች በማንዳ ሆስፒታል የሞቱ ሲሆን፣ 12ቱ ደግሞ በሞትና በህይወት መካከል እንደነበሩ መዘገባችን ይታወቃል። በጽኑ የቆሰሉ አዛዦችም ወደ መቀሌ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የግጭቱን መንስኤ እስካሁን በትክክል ለማወቅ አልተቻለም። በአካባቢው የተመደቡ የሰራዊት አባላትን ለማናገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም። በቡሬ ግንባር አካባቢ የሞባል ስልክ ኔት ወርክ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን መረጃዎን ያደረሱን ምንጮች ገልጸዋል።
ማንዳ ከቡሬ ግንባር 21 ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፣ ግጭቱ በትክክል የተነሰባት ቦታ አሊ ፉኑ ዳባ እየተባለ በሚጠራው የጎሳ መሪ ስም በተሰየመ አሊ ፉኒ አካባቢ ነው።