ታህሳስ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የመከላከያ ምንጮች እንደገለጡት በቡሬ ግንባር በሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ማንዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ማክሰኞ ሌሊት የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት እስከ እኩለቀን ዘልቆ እንደነበርና አሁንም ውጥረቱ እንዳለ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
የእርስ በርስ ጦርነቱ እንደተጀመረ የአካባቢው ነዋሪ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ጀመሩ በሚል ቀየውን ለቆ የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት በሄሊኮፕተር እየተንቀሳቀሱ ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል።
40 ወታደሮች መሞታቸውን እንዲሁም ከ39 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ከማንዳ ሆስፒታል የተገኘ መረጃ ያመለካተ ሲሆን፣ ሆስፒታል ሳይደረሱ የሞቱ፣ ወደ መቀሌ ሆስፒታል በሄሊኮፕተር የተወሰዱ ወታደራዊ አዛዦች መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሎአል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ 15 ወታደሮች ወዲያውኑ መሞታቸውን ፣ 12ቱ ደግሞ ለሞት ሲያጣጥሩ በአይናቸው ማየታቸውን አንድ ስማቸውም ድምጻቸውም እንዳይተላለፍ የጠየቁ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰሩ ነርስ ተናግረዋል።
የግጭቱን መንስኤ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም። አንዳንድ ወገኖች ግጭቱ በህወሀት ወታደራዊ ባለስልጣናት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ነው ሲሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ በህወሀት ደጋፊ ወታደሮችና በተቀረው ሰራዊት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ነው ይላሉ። ኢሳት የግጭቱን ትክክለኛ ምንጭ ለማወቅ ጥረት እያደረገ ነው።
ማንዳ ከቡሬ ግንባር 21 ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፣ ግጭቱ በትክክል የተነሰባት ቦታ አሊ ፉኑ ዳባ እየተባለ በሚጠራው የጎሳ መሪ ስም በተሰየመ አሊ ፉኒ አካባቢ ነው። ግጭቱ በዚሁ ስፍራ ይጀመር እንጅ ወደ አራት አጎራባች አካባቢዎች ተሰራጭቶ እንደነበር ምንጮች አመልከተዋል።
ከትናንት በስቲያ እና ትናንት ውጥረቱ እንደነበር ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ምናልባትም ግጭቱ እንደገና ሊያገረሽ ይችላል በሚል ስጋት የአካባቢው ሰዎች ቀያቸውን እየለቀቁ ነው።
የቡሬ ግንባር ዋና እዝ መቀሌ የሚገኝ ሲሆን፣ በሰሜን እዝ አዛዥ ጄነራል ሳእረ መኮንን እንደሚመራ ይታወቃል።
ቡሬ ግንባር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከባድመ ቀጥሎ ሀይሉን በብዛት ያሰማራበት ቦታ መሆኑ ይታወቃል። ኢሳት በቅርቡ በሰሜን ግንባር የተመደበን አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል በማናገር በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን ችግር መዘገቡ ይታወሳል።
በሌላ ዜና ደግሞ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሰው የአፋር ጋድሌ ሚሊሺያ ሀይል ወጣቶችን ትመለምላላችሁ የተባሉ የሚሊሺያው ወታዳራዊ አዛዥ የሆኑት የኮሎኔል ሙሀመድ አህመድ 4 የቅርብ ዘመዶች ተይዘው ታስረዋል። በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት መንገሱንና መንግስትም ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በርካታ ወታደሮችን ማስፈሩን መዘገባችን ይታወሳል።