በቡሬ ከተማ መንግስትን ይቃወማሉ የተባሉ ባለሃብቶችና ወጣቶች እየታሰሩ ነው ተባለ

ኢሳት (ጳጉሜ 4 ፥ 2008)

በአማራ ክልል በቡሬ ከተማ የተቀቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግስትን አይደግፉም የተባሉ ባለሃብቶችና ወጣቶች እየታሰሩ እንደሆነ ተገለጸ።

ባለሃብቶቹ የታሰሩት ነሃሴ 20 ህወሃት/ኢህአዴግን በመቃወም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመሳተፋቸው ሳይሆን ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የቡሬ ከተማ የፖሊስ አስተዳደር ጽ/ቤት  በከተማዋ የሚገኙ ባለሃብቶች የወደመባቸው ንብረት እንዲያሳውቁ በደብዳቤ ጠይቆ፣ ህዝባዊ ተቃውሞውን ያነሳሱ በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ገልጿል። የወደመባቸውን ንብረት በባለሙያ በማስገመት ለፖሊስ ጽ/ቤት እንዲያሳውቁ ሲል በደብዳቤው ጠይቋል።

ሰላማዊ ሰልፍ ሲካሄድ በነበረው ሁኔታ ንብረት የወደመባቸው ሆኖም ግን ጉዳያቸውን ወደፍርድ ቤት ለመውሰድ ፍላጎት ያላሳዩ ባለሃብቶችም ጭምር በህወሃት/ኢህአዴግ ሃይሎች እየተዋከቡ እንደሚገኙና ሁሉም ብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተወስደው መታሰራቸውን ለኢሳት ከደረሰው መረጃ መረዳት ተችሏል።

በዚህ የእስር ሂደት በከተማዋ የሚገኙ ታላላቅ ባለሃብቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል  ባለሃብቶችና ስራ-አስኪያጆች  እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

በቡሬ ከተማ ነሃሴ 20 በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ 6 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። በከተማው የትንሳዔ ሆቴል ባለቤትና የህወሃት ጽ/ቤት ሃላፊ የሆነው አቶ ተሻለ በርሄ ህወሃትን አይደግፉም ወይም አገዛዙን ይቃወማሉ ተብሎ የሚጠረጠሩ ሰዎችን እየጠቆመ በማሳሰሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ከሃገር ቤት ከደረሰን መረጃ መረዳት ተችሏል።