በቡራዩ ተፈጸመውን ወንጀል ያቀነባበሩ ግለሰቦች በአሸባሪነት ተከሰሱ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 28/2011) በቡራዩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያቀነባበሩና የፈጸሙ ግለሰቦች በአሸባሪነት መከሰሳቸው ታወቀ።

ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ከቡራዩ በመጡ ወጣቶች መካከል ግጭት እንዲከሰት በተለይ ፓስተር በተባለው የአዲስ አበባ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን አቃቤ ሕግ ገልጿል።

ከቡራዩ የመጡትን ወጣቶች በማደራጀትና ሽጉጥ በመተኮስ ግጭት እንዲከሰት ማድረጋቸውን በፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ያስረዳል።

በተጠርጣሪዎቹ ቤት 74 ገጀራና ቢላዋ መገኘቱም ተመልክቷል።

ሳምሶን ጥላሁን፣አለሙ ዋቅቶላ፣ቡልቻ ታደሰ፣ሃሺም አሚር፣ሽፈራው እና አሊ ዳንኤል የተባሉት 6ቱ ተከሳሾች በሳምንቱ መጨረሻ በፌደራሉ የመጀምሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት መቅረባቸውን የገለጸው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ግጭቱን በማነሳሳት፣በማስተባበርና ጥቃት ፈጻሚዎችን በመንግስት ተሽከርካሪ በማሸሽ አብይ ተዋናዮች መሆናቸውን አመልክቷል።

ተከሳሾቹ ወንጀሉን በማስተባበር፣በማነሳሳት እንዲሁም ገንዘብ በማከፋፈልና ሃሰተኛ መታወቂያ ከማዘጋጀት ባሻገር በተለይ አንደኛው ተከሳሽ የነዋሪዎችን መሬት እየቀማ፣ለሌሎች በመስጠት ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አቀባበል ወደ አዲስ አበባ የሚሔዱ የቡራዩ ወጣቶችን በማደራጀት ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል።

በተለይም ፓስተር ተብሎ በሚጠራው የአዲስ አበባ አካባቢ ከቡራዩ በመጡ ወጣቶችና በአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ግጭት እንዲነሳ ማድረጉና ሽጉጥ መተኮሱ ተመልክቷል።

ይህው ሳምሶን ጥላሁን የተባለው 1ኛ ተከሳሽ ቡራዩ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ብቻ 74 ገጀራና ቢላዋ እንደተገኘበትም መርማሪ ፖሊሱ ለፍርድ ቤት አስታውቋል።

ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉም አስተባብለዋል።

ከአእምሮ ሕሙማን ጋር ታስረናል ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው በዋስትና እንዲፈቱ የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ወንጀሉ የሽብር በመሆኑ ዋስትና አይፈቀድም ሲል ከልክሏል።

ችሎቱ ለጥቅምት 22/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።