በበለጸጉ አገራት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ውድቅ ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)

የአለም አቀፍ አረንጓዴ ከባቢ (ግሪን ክላይሜት) በጀት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ባሰበው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ላይ የበለጸጉ ሃገራት  ያቀረቡትን ተቃውሞ ተከትሎ ለኢትዮጵያ ሊለቀቅ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ውድቅ ተደረገ።

ከ20 የሚበልጡ የተቋሙ የቦርድ አባላት ሃሙስ ለሁለተኛ ቀን በቀጠሉት ውይይት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በነበረው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ላይ ሰፊ ልዩነት ማንጸባረቃቸውን ሮይተርስ ከደቡብ ኮሪያ ዘግቧል።

አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስዊዘርላድ፣ ስዊዲን፣ ጀርመን እና ጃፓን በኢትዮጵያ ተቃሞ ያቀረቡ ሃገራት መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ልማትና ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን እንደሚያከናውንና ከሁለት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ባቀረበው ፕሮጄክት አካትቶ እንደነበር ክላይሜት ሆም የተሰኘ የአካባቢ የዜና አውታር አመልክቷል።

ይሁንና የበለጸጉት ሃገራት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሃሳብ አሳማኝ አለመሆኑና በድርቅ የተጎዱ ሰዎችን በጥገኘነት ላይ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።

አብዛኛው የቦርድ አባላት ተቃውሞ በማቅረባቸው ምክንያት ግሪን ክላይሜት ፈንድ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረው የ100 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ውድቅ እንዲሆነ መደረጉን ለመረዳት ተችሏል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፕሮጄክት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት መቅረቱን የአካባቢ የዜና ወኪሉ ክላይሜት ሆም በዘገባው አስነብቧል።

ለኢትዮጵያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንዲለቀቅ ተቃውሞን ያቀረቡ አካላት አካባቢን መሰረተ ድርጎ ለአምስት አመት ይካሄዳል በተባለው ዙሪያ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው የዜና አውታሩ በዘገባው አስፍሯል።

የደሃ ሃገራት ተወካዮች እንዲሁ የገንዘብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ አልያም ለደሃ ሃገር ባለመሰጠቱ ቅሬታ እንዳደረባቸው ቢገልጹም የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው የልማት ሃሳብ ድክመት እንደታየበት አረጋግጠዋል ሲል ክላይሜት ሆም አክሎ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት በማህብረሰብ የሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በዋናነት በፕሮጄክቱ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ የግድብ ፕሮጄክቶችን አለማቅረቡ ታውቋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በሃገሪቱ የሚካሄዱ የግድብ ስራዎች የታዳሽ ሃይል እንዲሆኑ ቢገልጹም በሃሳቡ ያልተካተቱበት ምክንያት አልተገለጸም። በደቡብ ኮሪያ ለሶስት ቀን ጉባዔው ሲያካሄድ የነበረው ግሪን ክላይሜት ፈንድ ከተለያዩ ሃገራት ለቀረቡ ስምንት የልማት ፕሮጄክቶች የ755 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አፅድቋል።

በደቡብ ኮሪያ የተገኙ የኢትዮጵያ ተወካዮች ከበለጸጉ ሃገራት ስላቀረበው ተቃውሞ የሰጡት ምላሽ የለም።