በበለና እና በአማሮ ወረዳዎች መካከል በተነሳ ግጭት የዜጎች ህይወት እያለፈ ነው

ሚያዝያ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት በደቡብ አካባቢ በሰገን ዞን በአማሮ ወረዳ እና አጎራባች በሆነው በጉጂ ዞን ውስጥ በሚገኘው በላና ወረዳ በተነሳ ግጭት የዜጎች ህይወት እያለፈ ነው።
በአካባቢው የተነሳውን ከፍተኛ ድርቅ ተከትሎ በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦች ለእንስሳት መኖና ውሃ በማጣታቸው ከአካባቢው አካባቢ መሰደዳቸውን ተከትሎ የተፈጠረ ግጭት መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ ከተጀመረበት ካለፉት 4 ቀናት ጀምሮ በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ የበርካታ ዜጎች ህይወት አልፏል። የሟቾችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባይቻልም፣ ከሁለቱም ወገኖች ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች መሞታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ ግጭቱ አሁንም በመቀጠሉ ሌሎች ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ምክንያት እየሆነ ነው።
በአካባቢው የሚታየውን ድርቅ ተከትሎ እስካሁን የተላከው እርዳታ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በተለይ የውሃ እና የእንስሳት መኖ እጥረቱ በከብት እርባታ በሚተዳደረው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር በርካታ ማህበረሰቦችን እየጨመረ ግጭቱ እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል እነዚህ ነዋሪዎች አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በርሀቡ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል። ከወራት በፊት 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው መሰረት 2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመገለጹ፣ የተረጅዎች አሃዝ ወደ 7 ሚሊዮን 700 ሺ ከፍ ብሎአል።
የውሀ እጥረት በብዛት በታየባቸው በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ድርቁ ማየሉ ተገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እጥረቱን ተከትሎ ወረርሽኝ ሊነሳ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
አንድ አርሶአደር በእድሜያቸው አይተውት በማያውቁት ድርቅ 700 በጎችና ፍየሎች በውሀ እጥረት እንደሞቱባቸው ለኦክስፋም ተናግረዋል።
በኬንያ 2 ሚሊዮን 700 ሺ፣ በሶማልያ 2 ሚሊዮን 900 ሺ፣ በዩጋንዳ 1 ሚሊዮን 600 ሺ ሰዎች በምግብ እጥረት ተጠቅተዋል። በኢትዮጵያ የተረጅዎች ቁጥር ከተጠቀሰው አሃዝ ሊልቅ ይችላል የሚል ስጋት አለ።