ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልል በቋራ ወረዳ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የመስከረም ወር ደሞዝ በወቅቱ ስላልደረሰላቸው ትናንትና ዛሬ የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። ተቃውሞአቸውንም ለመንግስት ባለስልጣናት አቅርበዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ መምህር ለኢሳት እንደገለጡት ፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህራን ከሀምሌ ወር ጀምሮ ደሞዝ ያልተከፈላቸው በመሆኑ፣ “ካልበላን አንሰራም” በሚል ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋትና ተማሪዎችን ለመበተን ተገደዋል። የመንግስት ባለስልጣናት መምህራን ስራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ ለማግባባት ጥረት እያደረጉ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአስተዳዳር ሰራተኛ ተናግረዋል።
ፖሊሶችን ጨምሮ ሌሎችም የመንግስት ሰራተኞች በተቃውሞው መቀላቀላቸው ታውቋል። የመንግስት ባለስልጣናት ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ያልተከፈለው ከቦታው እርቀት አንጻር መሆኑን ይናገራሉ። የመንግስት ሰራተኞች በበኩላቸው፣ ከአስተዳዳሩ ባለስልጣናት ገንዘብ የለም ተብሎ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።