በቆዳና ውጤቶች ምርት ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ አንድ የብሪታኒያ ኩባንያ ገቢው ክፉኛ መጎዳቱን ይፋ አድረገ

ኢሳት (ታህሳስ 12 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ምርት ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ አንድ የብሪታኒያ ኩባንያ በክልሉ ሲካሄድ በቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በተያዘው በጀት አመት ገቢው ክፉኛ መጎዳቱን ረቡዕ ይፋ አድረገ።

ፒታርድስ የተሰኘው ይኸው ግዙፍ ኩባንያ ያጋጠመውን የምርትና የትርፍ መቀነስ ተከትሎም የድርጅቱ የአክሲዮን ድርሻ በ14 በመቶ ማሽቆልቆሉን ድርጅቱ በድረ-ገጹ ላይ አስፍሯል።

በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ በቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በምርቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ያወሳው ፒታርድስ፣ የደረሰበትን የምርት መስተጓጎል ለማመጣጠን በብሪታኒያ ምርቱን ለማምረት ተገዶ እንደነበርም አስታውቋል።

ይሁንና ኩባንያው በአመት ዕቅዱ ለማምረት የያዘው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት በሚፈለገው መጠን ሊቀርብ ባለመቻሉ በበጀት አመቱ ገቢው ክፉኛ መጎዳቱን ገልጿል። ኩባንያው የደረሰበትን የገቢ መቀነስ በመጠን ከመጥቀስ የተቆጠበ ሲሆን፣ የአክሲዮን ድርሻ ገቢ ግን በ14 በመቶ መቀነሱን አረጋግጧል።

ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከውጭ ኩባንያዎች በተጨማሪ የመንግስት የውጭ ንግድ ገቢ መጎዳቱን የንግድ ሚኒስቴር ሲገልፅ ቆይቷል።

የአለም ባንክ በበኩሉ በውጭ ንግድ ገቢው መቀነስ የተነሳ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያድግ ይችላል ከተባለው ከ11 በመቶ በላይ ወደ ስምንት በመቶ አካባቢ መቀነሱን ይፋ አድርጓል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ዕልባት የሚያገኝ ከሆነም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕደገት በፍረንጆች 2017 አም ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ባንኩ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በሶስት በመቶ አካባቢ መቀነስን ያስመዘገበ ሲሆን፣ ድርጊቱ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ተነግሯል።