በቆሸ ከደረሰው እልቂት ጋር በተያያዘ ድጋፍ ያላገኙ ቤተሰቦች መኖራቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናገሩ

ግንቦት ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሸ እየተባለ በሚጠራው የቆሻሻ መድፊያ ቦታ ላይ ቆሻሻ ተንዶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ካጠፋ በሁዋላ፣ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የገንዘብ እርዳታ ለግሰዋል። የገንዘብ ድጋፉ ገዢው መንግስት በበላይነት በሚቆጣጠረው የባንክ አካውንት እንዲገባ ከተደረገ በሁዋላ፣ ገንዘቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለተጎጂ ቤተሰቦች አልተከፋፈለም ነበር። ይህ ሁኔታ በተጎጂ ቤተሰቦችና እርዳታ በለገሱ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ማስነሳቱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሚዲያዎች “ ገንዘቡ የት ገባ ? “ የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ሰንብተዋል።
ኢሳት ከአንዳንድ የተጎጂ ቤተሰቦች ባሰባሰበው መረጃ መሰረት ገዢው ፓርቲ በቅርቡ ለእርዳታ ከለያቸው 16 ቤተሰቦች ውስጥ ለ7ቱ ገንዘብ ማከፋፈሉንና 9 ቤተሰቦች እስካሁን እርዳታ እንዳልተሰጣቸውም። እነዚህ ቤተሰቦች እርዳታ ለምን እንዳላገኙ ግልጽ የሆነ ነገር የለም። ቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው ተነግሮአቸው የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ቤት ያገኙ ሰዎች የሉም።
በሌላ በኩል ለ16 ቤተሰቦች የሚሰጠው ገንዘብ፣ ተዋጣ ከሚባለው አጠቃላይ ገንዘብ ጋር ሲነጻጻር እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ቀሪው ገንዘብ የት ሊገባ ነው የሚል ጥያቄ አስነስቷል። በአጠቃላይ ለተጎጂ ቤተሰቦች በድምሩ እስከ 16 ሚሊዮን ብር እንደሚጣቸው ቃል የተገባ ሲሆን፣ የተዋጣውና ቃል የተገባው ገንዘብ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር መሆኑ ሲታይ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ለምን አገልግሎት እንደሚውል የታወቀ ነገር የለም። ገንዘብ የለገሱ ወገኖች ገዢው ፓርቲ፣ በአጠቃላይ የተለገሰውን ገንዘብና ለህዝብ የተከፋፋለውን ገንዘብ ይፋ እንዲያደርግ እየጠየቁ ነው።
መረጃዎች በግልጽነት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲቀርቡ የሚጠይቁት እነዚህ ወገኖች፣ ገዢው ፓርቲ የጉዳቱን መንስኤ አጥንቼ አሳውቃለሁ ባለው መሰረት ቶሎ እንዲያሳውቃቸውም ጠይቀዋል።