ሐምሌ ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ወኪላችን እንደዘገበው ባለፉት ሁለት ቀናት በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በቆላ ድባና በገጠር አካባቢዎች በሰማራት በህዝቡ ላይ ድብደባ ከመፈጸም ጀምሮ አንዳንዶችን ይዘው በማሰር ላይ ናቸው።
ባለፈው አመት የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሳይቋረጥ ከቀጠለባቸው የሰሜን ጎንደር ከተሞች መካከል ቆላ ድባ አንዷ ስትሆን፣ በአካባቢው የሚካሄደውን የትጥቅ ትግል ተከትሎ አካባቢው አመቱን ሙሉ በውጥረት አሳልፏል። ባለፉት ሁለት ቀናት አርሶአደሮች ዱላቸውን እየተቀሙ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። ህጋዊ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ተቀምተው የታሰሩ አርሶአደሮችም አሉ። ወጣቶች እንደልብ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉም ተናግረዋል።
በትጥቅ ትግል እተፋለሙ ላሉ ሃይሎች የተለያዩ ድጋፎችን ታደርጋላችሁ በሚል መምህራን እና አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች ተይዘው ታስረዋል።
በዞኑ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለው በአርሶአደሩ ላይ ነው። በርካታ አርሶአደሮች እስር ቤት በመግባታቸውና አፈናውን በመፍራት በመሰደዳቸው ማሳቸው ጾም አድሯል።