በቆላድባ አንድ ወታደር የ14 ዓመት ልጃገረድ መድፈሩን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞውን አሰማ

ሚያዝያ ፩ (አንድ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአካባቢው የሚታየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ከተላኩት ወታደሮች መካከል አንዱ የሆነው ለጊዜው ስሙ ያልታወቀው ወታደር፣ እሁድ ሚያዚያ 1 ፣ ከጓደኛው ጋር በመሆን አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ በጉልበት ወስዶ ደፍሯታል። ታዳጊዋ ደም እየፈሰሳት ለአካባቢው ሰዎች መናገሩዋን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞውን እያሰማ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርቷል።
ሰቀልት ክፍል ወይም ቀበሌ ዜሮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነቸው ታዳጊ ልጃገርድ፣ ወደ ቤቷ ልትገባ ስትል በወታደሮች ታፍና ግርማ ድልድይ በሚባል አካባቢ ተወስዳ ከተደፈረች በሁዋላ፣ ደም እየፈሳሳት ወደ ቤተሰቦቿ ሄዳ አልቅሳ በመናገሯ፣ የአካባቢው ነዋሪ በቁጣ ወደ መስተዳድሩ ያመራ ሲሆን፣ የመስተዳድሩ አባላትም ለጊዜው ወታደሮቹ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳልሆኑ ቢናገሩም ፣ በመጨረሻ የህዝቡን ቁጣ በማየት ሁለቱም እንዲታሰሩ አድርገዋል።
ታዳጊዋን የደፈረው ወታደርና ባልደረባው በህዝቡ ግፊት ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ህዝቡ ግን ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳለውና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በዚሁ ከተማ ባለፈው ቅዳሜም እንዲሁ በከብት ገበያ ላይ አርሶአደሮች ተጨማሪ የከብት ግብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተከትሎ፣ አርሶአደሮች ባሰሙት ተቃውሞ አንድ ፖሊስ ተደበድቦ ሆስፒታል ገብቷል። አዲሱ መመሪያ አርሶአደሮች ለሽያጭ ላመጡዋቸው የእርድ እንስሳት 10 ብር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ ይከፍሉት ከነበረው ክፍያ ላይ አዲሱ መመሪያ 7 ብር ጭማሪ እንዲከፈል ያዛል። አርሶአደሮች ለወራት ሲቃወሙት ቢቆዩም መልስ የሚሰጣቸው በማጣቱ፣ ጉዳዩ ተካሮ ባለፈው ቅዳሜ ለተቃውሞ መነሻ ሆኗል። አርሶአደሩን በግድ ለማስከፈል ከሄዱት ፖሊሶች መካከል አንዱ በጽኑ ተደብዶ ሆስፒታል ገብቷል። ጉዳዩ ግን አሁንም እልባት አላገኘም።