በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ (ቢጂአይ) ውስጥ ምዝበራው ተባብሶ መቀጠሉ ተነገረ፡፡
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 11 ቀን 2010 ዓ/ም ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በህወሃት ሰዎች እጅ ለዘመናት በቁጥጥር ስር መዋሉን ለመከላከል የሚሞክር አመራር በመጥፋቱ፤ ምዝበራው አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን ሰራተኞች ናቸው የተናገሩት።
መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም የኢሳት ቴሌቪዥን ፋብሪካው በህወሃት አባላት ቁጥጥር ስር መሆኑን የውስጥ አዋቂ ታማኝ ምንጮችን ጠቅሶ ባቀረበው ዜና ፤የፋበብሪካው አመራሮች ከፍተኛ መደናገጥ እና ትርምስ ውስጥ ገብተው እንደነበር የገለጹት ታማኝ ምንጮች፤ ኃላፊዎቹ፦”መረጃ የሰጠ ማን ነው?” በማለት ሰራተኞችን ሰብስበው ሲያስጨንቁ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ከኢሳት ዜና በኋላ “መረጃ ሰጥተዋል” ተብለው የተጠረጠሩ ሰራተኞችን -የህወሃት ከፍተኛ የደህንነት ሰዎች ወደ እስር ቤት ያስገቧቸው ሲሆን ፤በሰራተኞች ላይም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ድብደባ ሲያካሂዱ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከዘገባው በኋላ አሰራራቸውን ስውር ለማድረግ ዝቅተኛ የኃላፊነት ቦታዎችን ሳይቀር ምስጢር በሚጠብቁ የህወሃት አባላት በማጠናከር ዝርፊያውን በስውር ማድረጋቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በፋብሪካው ውስጥ ያለው የስልጣን ክፍፍል፤ ደንብና ስርዓትን ጠብቆ ሰራተኞችና ኃላፊዎች በችሎታቸው የሚመደቡበት ሳይሆን ፤በቋንቋ፣ በትውልድና ዘርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፤ በአብዛኛው የፋብሪካው ሰራተኞች ላይ በደል እየደረሰ መሆኑን ሠራተኞች በምሬት ይገልጻሉ፡፡
በፋብሪካው ውስጥ በከፍተኛ አመራር ላይ የተቀመጡት የህወሃት አባላት የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ካባባሱት መካከል እንደሚደመሩ የሚገልጹት ውስጥ አዋቂዎች፤ እነዚህ ኃላፊዎች ለፋብሪካው ያስፈልጋሉ በሚባሉ ጥቃቅን የመለዋወጫ ዕቃዎች ሰበብ ከፍተኛ ምንዛሬ ወደ ፈረንሳይ እንዲጓጓዝ በማድረግ ደባ እንደሚፈጽሙ በፋብሪካው ከሃያ ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሰራተኞች ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በአስር ብር የምትሸጥ አንድን “ቡሎን”- ፋብሪካው ከፈረንሳይ ሃገር በሰላሳና አርባ ዶላር ገዛሁ በማለት ገንዘቡ ተመንዝሮ ወደ ፈረንሳይ እንዲጓዝ ከፍተኛ አሻጥር በሃገሪቱ ላይ እየተሰራ መሆኑን ያጋለጡት የቴክኒክ ሰራተኞች ፤አዲሱ የዶክተር አብይ አስተዳደር የፋብሪካውን አጠቃላይ አሰራር እንዲፈትሽላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኩባንያው ተቆርቋሪ ምንጮች ቀደም ሲል በቀረበው የኢሳት ዜና ያጋለጡት የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢሳያስ አደራ ለማስተዋቂያ በሚል ወደ ፋብሪካው ተገዝተው ከገቡ በኋላ ለደንበኞች በስጦታ ለሚሰጡ ልዩ ልዩ ወንበሮች ፣ብርጭቆዎች፣ ጠረጴዛዎች እንዲሁም በሚሰሩ ቢል ቦርዶች እና ልዩ ልዩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች በሚካሄደው የጫራታ ሂደት ከፍተኛ ሃብት ማከበታቸው ተነግሯል።
ግለሰቡ ከቢጂአይ ኩባንያ ጋር በርካታ የማስታወቂያ “ባነሮችን” እና በፋብሪካው ውስጥ ለሚያገለግሉ መኪኖች የሚለጠፉ ስቲከሮችን ለረጂም ጊዜ በመስራት የሚታወቀው “ፓንተር” የተባለው ድርጅት ባለቤት መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።
አቶ ኢሳያስ በዙሪያቸው ባሉ የህውሃት አባሎች በመታገዝ በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከኩባንያው ከመዝረፋቸው ባሻገር በቅርቡ ፋብሪካው ለመግዛት ባሰበው “ዘቢደር ቢራ” የፕሮሞሽን ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል፡፡
የዘቢደር ቢራን ለመጠቅለል እንቅስቃሴ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ፤በቀጣይ በአዲሱ ፋብሪካው ላይ ለሚያደርገው ማስፋፊያ ከፍተኛ በጀት በማስመደብ ለከፍተኛ የህወሃት አመራሮች የዝርፊያ መንገዱን ለማመቻቸት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
ኩባንያውን በፋይናንስ ኃላፊነት በመምራት ላይ የሚገኙት ሌላው የህወሃት አባል አቶ ቴዎድሮስ አሁንም ቦታቸው ላይ ሆነው የህወሃትን አባላት ጥቅም ለማስከበር ሌት ተቀን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
አቶ ቴዎድሮስ የኩባንያውን ምርቶች ከቦታ ቦታ የሚያጓጉዙ ከባድና ቀላል መኪኖችን በኮንትራት ለማሰማራት ከባለንብረቶች ጋር በሚያደርጉት ያልተገባ ድርድር ከፍተኛ ዝርፊያቸውን አሁንም አጠናክረው መቀጠላቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።
አቶ ቴዎድሮስ ወደ ድርጅቱ ሲገቡ ምንም ሃብት ያልነበራቸው ሲሆን፣ በህገወጥ መንገድ ባገኙት ገንዘብና የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ባመቻቹላቸው መንገድ ተጠቅመው ከሃያ በላይ “ኢሮ ትራከር” በመባል የሚታዎቁ ከባድ የጭነት መኪናዎችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት አብዛኛውን የኩባንያው ምርቶች በማመላለስ ከፍተኛ ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን ቀደም ባለው ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡
ግለሰቡ በኩባንያው ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የባለቤታቸውን ቤተሰቦች ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን በማስያዝ ኩባንያውን የቤተሰብ ድርጅት እንዲሆን ማድረጋቸውን የኢሳት ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ኩባንያውን በበላይነት ከተቆጣጠሩት የህወሃት አባላት መካከል ሌላው የፋብሪካው የአስተዳደር ኃላፊ በመሆን ትልቁን ሚና የሚጫወቱት አቶ ፍትሀነገስት በአስተዳደሩ ውስጥ የህውሃት አባላትን ከዘበኝነት አንስቶ ያለ ችሎታቸው ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ያልተገባ ጥቅም እንዲያካብቱ በማድረግ በሰራተኛው መካከል ከፍተኛ አድልዎ መፈጸማቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
አስተዳዳሪው በስራ ድክመት የሚወርዱ የህውሃት አባሎች ተመልሰው ወደ ላይ እንዲወጡ እና የሌሎች ብሄር ተወላጆች ምንም አይነት እድገት እንዳያገኙ በማድረግ ሲፈፅሙት የነበረውን የዓመታት ስራቸውን አጠናክረው እየፈጸሙ መሆኑን ምንጮች ያክላሉ።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለረጅም ጊዜ የሰሩ ምንጮች እንደሚናገሩት አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በዘረፋ በተሳሰሩ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እጅ ላይ ወድቋል።
“የዶክተር አብይ መንግስት መብታችንን ሊያስከብርልን ይገባል” የሚሉት ሰራተኞች፤ ዜጎቹ በአንድ ቡድን የበላይነት ከፍተኛ ሰቆቃና የመብት ረገጣ ሲፈጸምባቸው ፤ዝምታን የሚመርጥ መንግስት እንደማይኖር እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡