በቅርቡ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦችን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)

በደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢ በቅርቡ የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች ህይወትን አደጋ ላይ እንደጣለ  ተመድ ገለጸ።

በአካባቢው የተከሰተውን ይህንኑ አዲስ የድርቅ አደጋ ተከትሎ በቤት እንስሳት ላይ አሉታዊ ጉዳት መከሰት መጀመሩን ያስታወቀው ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል 10 በመቶ የሚሆኑ የአርብቶ አደሩ እንስሳቶች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት እንደሚፈልጉ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ይኸው የድርቅ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘም በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የከፋ አደጋ ያደርሳል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የሶማሊ እና የኦሮሚያ በርካታ ዞኖች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው ተውቋል።

በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን ብቻ ወደ 400 ሺ የሚጠጉ የቤት እንስሳት አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ካላገኙ ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ባለፈው አመት በሃገሪቱ ስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት መሞታቸውን ድርጅቱ አውስቷል።

በአዲስ መልክ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሰዎች ላይ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን ጉዳት ለመተንበይ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማትን ያካተተ የባለሙያዎችን ቡድን በአካባቢው ጥናት እያካሄደ እንደሆነ ለመረዳት ተልችሏል።

ይኸው አዲስ የድርቅ አደጋ ከኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ በደቡብ የክልል በሰውና በቤት እንስሳቶች ላይ ተመሳሳይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።

በክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የአለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (FAO) የእንስሳት ህይወትን ለመታደግ የ14 ሚሊዮን ዶላር (የ300 ሚሊዮን ብር አካባቢ) የእርዳታ ጥሪን አቅርቧል።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ እልባትን ባለማግኘቱ ምክንያት በአሁኑ ወቅት 9.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙ ታውቋል።