በቅርቡ በጎንደር በሚከበረው የከተሞች ቀን በክልሉ ያለውን ድባብ እንዲቀይር ብዓዴን ሃላፊነት ተሰጠው

 

ኢሳት (መጋቢት 19 ፥ 2009)

በሚመጣው ሚያዚያ ወር በጎንደር የሚከበረው የከተሞች ቀን የክልሉን ገጽታም ሆነ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ድባብ እንዲቀይር ለብዓዴን ሃላፊነት ተሰጠው።

ምክትል ጠ/ሚ/ ደመቀ መኮንን ሂደቱን በበላይነት እንዲያስተባብሩ መሾማቸውም ታውቋል። ዝግጅቱ እንደ መስቀልና ጥምቀት በዓላት የፈዘዘ እንዳይሆን ሁሉም የብዓዴን አባላት የክልሉ መንግስት በሙሉ አቅማቸው እንዲንቀሳቀሱም ከፌዴራል መንግስት መመሪያ መተላለፉን መረዳት ተችሏል።

ከሚያዚያ 21 ቀን 2009 ጀመሮ በጎንደር በሚከበረው የከተሞች ቀን ለመሳተፍ ከሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች 20ሺ ሰዎች ጎንደር እንደሚገቡ የተረጋገጠ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት ለእንግዶቹ ሆቴሎችን እንዲያመቻችና ወጪውንም እንዲሽፍንም ሃላፊነት ተጥሎበታል።

በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በአማራ ክልል የተቀጣጠለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነችው ጎንደር የሚከበረው በዓል ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሰላም መስፈኑን ማሳየት ይቻላል የተባለው ዝግጅት ደማቅ እንዲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የጎንደር አቻ ወይም እህትማማች ከተማ ተወካዮችም ተጋብዘዋል።  በውጭ ሃገር የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በይበልጥም የጎንደር ተወላጆች እንዲገኙ ጥሪ እንዲደረግም ብዓዴኖች ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ጠ/ሚ/ሩ ይገኙበታል የተባለው ይህ ዝግጅት በጎንደር ሰላም መሆኑን ካሳየንበት፣ ሁሉም የሃገሪቱ ክልል ሰላም ለመሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣል በሚል በከፍተኛ ዕቅድና ዝግጅት ቀጥሏል። ዝግጅቱ በመስቀል እና በጥምቀጥ በዓል ላይ የታየው የፈዘዘ ሁኔታ እንዳይደገም ለብዓዴን መሪዎች ከፌዴራል ማሳሰቢያ መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሏል። የጸጥታውን ሃላፊ የፌዴራል መንግስት እንደሚመድብ ተመልክቷል።