(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 2/2009)የአማራና ቅማንትን ማህበረሰብ ለመለያየት በሚሰጠው ሕዝበ ውሳኔ ተጽእኖ ለማድረግ በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ ካድሬዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች እየደበደቡና እያንገላቷቸው መሆኑ ተነገረ።
በሕዝቡ ውስጥ አማራና ቅማንት አይለያዩም በሚሉ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ላይ የግድያ ዛቻ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የጎንደር ሕብረት ገልጿል።
የሕብረቱ ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ንጋቱ እንደገለጹት መስከረም 7/2009 የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን የአማራና የቅማንት ማህበረሰብ መቼም አይነጣጠልም።
የአማራና የቅማንትን ማህበረሰብ ለመለያየት በጎንደር 12 ቀበሌዎች የሚካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።
የምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ግን በምዝገባ ሂደቱ ከፍተኛ ፈተና እንደገጠማቸው ነው የሚነገረው።
ቅማንትም ሆነ አማራ በክልል አይለያዩም በሚል በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የ12ቱ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ፍላጎት እንደሌላቸው የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።
በተለይም በጭልጋ አውራጃ ቋራና መተማ አካባቢ እንዲሁም በጎንደር ከተማ ምዝገባው በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም ተብሏል።
የጎንደር ሕብረት ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ንጋቱ ለኢሳት እንደገለጹት በሕዝበ ውሳኔው የአካባቢው ሕብረተሰብ አማራ ነኝ እንዳይልና እራሱን በቅማንትነት እንዲገልጽ እየተገደደ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሕወሃት ካድሬዎች አካባቢውን በቅማንትነት ከለዩ በኋላ ወደ ትግራይ ለመጠቅለል በግማሽ ትግራይና በሌላ ወገን ደግሞ ቅማንት የሆኑ ሰዎችን በቀስቃሽነት ይጠቀማሉ ነው ያሉት የጎንደር ህብረት ስራ አስፈጻሚው አቶ አበበ ንጋቱ።
እናም ህዝቡን በመከፋፈል የተጠመዱ የሕወሃት አጋፋሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አቶ አበበ አሳስበዋል።
እንደ አቶ አበበ ንጋቱ ገለጻ ሐገርና ህዝብ መቼም ቢሆን ይኖራሉ።የሕወሃት አገዛዝ ግን ሊወገድ እየተቃረበ ነው ብለዋል።
እናም አሉ አቶ አበበ የሕዝቡ ውሳኔ ውጤት ምንም ይሁን ምን አማራና ቅማንት መቼም ቢሆን የሚለያይ ሕዝብ አይደለም።
በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ተመሳሳይ አቋም ነበራቸው።
የአቶ ገዱ አቋም ግን ሙሉ በሙሉ ተገልብጦ የሕወሃትን አቋም እንዲያራምዱ ተገደዋል።