በቃፍቲያ ወረዳ የሚኖሩ የወልቃይት ተወላጆች በትግራይ ክልል ስር አንተዳደርም አሉ

ኢሳት (ግንቦት 9 ፥ 2008)

በትግራይ ክልል የሚገኙ ከአራት ሺ በላይ የቃፍቲያ ሁመራ አካባቢ የወልቃይት ተወላጆች በትግራይ ክልል ስር አንተዳደርም በማለት ሰኞ አዲስ የቃለ መሃላ ውሳኔ አስተለለፉ።

በተወላጆቹ ሲነሳ የቆየው አስተዳደራዊ ጥያቄ ፍትሃዊ ምላሽን ባለማግኘቱ ምክንያትም አካባቢው አሁንም ድረስ በውጥረት ውስጥ መሆኑን የአካባቢው ተወላጆች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስተድተዋል።

ከትግራይ ክልል ሃላፊዎች እየደረሰባቸው ያለው ጫናና ግፊት እየተጠናከረ መምጣቱን የሚናገሩት የቃፍቲያ አካባቢ ነዋሪዎች ሰኞ የተወሰደው ቃለመሃላ በአካባቢው ተወላጆች ላይ ያለፍላጎት የተወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ለማስቀረት ያለመ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ይሁንና በወልቃይት ተወላጆች የተወሰደውን ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ዳንሻን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች የጸጥታ ሃይሎች በአዲስ መልክ መስፈር መጀመራቸውን ነዋሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

አስተዳደራዊ የመብት ጥያቄን በማንሳታቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት ሰዎች አሁንም ድረስ አለመፈታታቸውን የተናገሩት እማኞች እየተደረገባቸው ያለን ጫናን በመቃወም ነዋሪዎች የእርሻ ስራና ትምህርታቸውን አስተጓጉለው እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው በሚገኙ የእምነት ተቋማት በአማርኛና በግዕዝ ሲካሄድ የነበረው ሃይማኖታዊ ስነስርዓትም በትግርኛ ቋንቋ እንዲካሄድ ትዕዛዝ መተላለፉን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የተወላጆቹ የስራ ቋንቋ እንዲቀየር እየተደረገ እንደሚገኝ ያስታወቁት ነዋሪዎች ሰኞ በነዋሪዎች የተላለፈው ቃለመሃላ ይህንኑ ጫና ለማስቀረት ያለመ እንደሆነ አክለው አስታውቀዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት የወልቃይት ተወላጆች ያነሱት የማንነት ጥያቄ ህጋዊ ምላሽን አግኝቷል ቢሉም በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ግን ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘቱንና አለመረጋጋት መስፈኑን ለኢሳት ተናግረዋል።

በክልሉ የተነሳውን የማንነትና አስተዳደራዊ ጥያቄ ተከትሎ በስፍራው ሲካሄድ በቆየ ተደጋጋሚ ግጭት በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውና ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።