በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች በተናጠል እየተሰቃዩ ነው። በእነ ወ/ት ንግስት ይርጋ ላይም የሃሰት ምስክር ሊቀርብ ነው

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ በደል እየተፈፀመባቸው መሆኑን ምንጮች አስታወቁ። እስረኞች የደንብ ልብስ እንዲለብሱ የሚገደዱት ወደ ቤተሰብ ሲወጡና ተነስተው ሲዘዋወሩ ብቻ ቢሆንም፣አሁን ግን የተኙ እስረኞች ሳይቀር የደንብ ልብስ አለበሳችሁም እየተባሉ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ እና የአመክሮ እስራት ጊዜ እንዲቀሙ ተደርገዋል።
ማንገላታቱ እና አካላዊ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው መካከል የፖለቲካ እስረኞች በቀዳሚነ ተርታ ይመደባሉ። እነዚህ እስረኞቹ ተለይተው ከፍተኛ ድብደባ ይፈፀምባቸዋል፣ ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸዋል፤ ካለጥፋታቸው ከአልጋ ወርደው መሬት ወለል ላይ እንዲተኙም ይደረጋሉ።
በእስር ቤቱ የፍርደኞች ክፍል በተለምዶ 6ኛ ቤት በመባል በሚጠራውና አምስት ክፍሎች ባሉት ክፍሎች የሚፈጸመው ሰቆቃ ከሁሉም የከፋ ሲሆን የጸሃይ ብርሃን እንዳያገኙም ይዘጋባቸዋል። ታንከር በመባል በሚታወቀው ክፍል የሚገኙት እነ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ እንዲሁም በዞን አራት የሚገኙት እነ ዶክተር መረራ ጉዲና ከፍተኛ ወከባ እና እንግልት ከሚፈጸምባቸው ውስጥ ይገኙበታል።
በስምንቱም የእስር ቤቱ ዞኖች ውስጥ ከዋና እስከ ምክትል አስተዳዳሪነት፣ የምርመራ ደህንነት ኃላፊነት፣ እስረኞችን ወደ ፍርድ ቤት በበላይነት የሚወስዱ አዛዦች፣ የለሊት የዙሪያ ጥበቃ ሃላፊዎች፣ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጫምሮ ሌሎችን የፖለቲከኛና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚጠብቁ ልዩ የጥበቃ ሰራተኞች እና አጃቢዎች በሙሉ የትግራይ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ጋር በተያያዘ ሕዝቡን ያነሳሳሉ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ግለሰቦች ላይ ያነጥጠሩ የጅምላ እስራቶች በኮማንድ ፖስቱ መፈጸማቸው ይታወሳል። በእስራት ሰለባ ከሆኑት አንዷ የሆነችውና ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ሰቆቃ እየተፈጸመባት ያለችው ወጣት ንግስት ይርጋ ላይም የሃሰት ምስክሮች ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ታውቋል።
ከሳሽ የሆነው አቃቤ ሕግ በተባለው የጊዜ ገደብ ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻሉ በተራዘመ የጊዜ ቀጠሮ ከመጉላላታቸው በተጨማሪ በእርሷና ከእርሷ ጋር በአንድ መዝገብ በተከሰሱት የሃሰት ምስክር እየተዘጋጀባቸው መሆኑን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ተናግረዋል። የፌደራል አቃቤ ህግ መጀመሪያ ከተያዙበት አካባቢ ምስክር እንደሚያመጣ ቢያሳውቅም፣ አሁን ግን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ የሃሰተኛ ምስክሮችን ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው እንዳሳዘናቸው ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ አባልና 5ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ በላይነህ ዓለምነህ ”ህወሓት ኢህአዴግ የሰላማዊ ትግሉን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ከየ አካባቢያችን አሰሮ አመጣን እንጅ የሰራነው ወንጀል የለም። በርካታ ዜጎች እየታሰሩ፣አገር በኮማንድ ፖስትና በወታደር እየተመራች ነው፡፡” ሲሉ ከህግ አግባብ ውጪ መያዛቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል።

አቶ በላይነህ ዓለምነህ ”ባልመረጡት አካል መገዛት እስር ነው፡፡ በአካል ሳንታሰርም ስቃይና መከራውን እናውቀዋለን፡፡ አሁንም በአቃቤ ህግ ተጨማሪ ግፍ እየተፈጸመብን ነው፡፡ ፍትህ አጥተናል” ሲሉ እየደረሰባቸው ያለውን ሰቆቃ ለፍርድ ቤቱ በዝርዝር አቅርበዋል።
አቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ምስክር አመጣለሁ የሚል አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን በመደርደር ምስክር ሊያቀርብ አለመቻሉን ፍርድ ቤቱ ቢያውቅም ፍርድ ቤቱ ግን አቃቤ ሕግን የማዘዝ አቅሙ ደካማ መሆኑን እና በዛም ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።